ከሰሞኑ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጅንካ አካባቢ የተከሰተውን እና የጤና ባለሙያዎችን ጨምሮ በበሽታው የተያዙ ሰዎችን ለህልፈት የዳረገውን በሽታ በሚመለከት ለሚዲያ መረጃ በመስጠታቸው ከስራ የተሰናበቱትን የጅንካ አጠቃላይ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር በሚመለከት የጤና ሚንስቴር መረጃው የለንም ሲል አስታውቋል፡፡
የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ ስለ ባለሙያው መባረር ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፣ “ባለሙያው ስለመባረሩ የምናውቀው ነገር የለም”፤”ጉዳዩ በእኛ ተቋም አይደለም የሚታየው” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። ሚኒስትሯ አክለውም “የህብረተሰብ ጤና ስጋት መረጃ አሰጣጥ የሚል ስርዓትና ፕሮቶኮል ስላለው በክልሉ በዛው የሚፈታ ጉዳይ ነው” በማለት፣ ዶክተሩ የተሰናበቱበትን ጉዳይ የፌዴራል ጤና ተቋም ኃላፊነት እንደማይወስድበት አመልክተዋል።
የጂንካ አጠቃላይ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር የነበሩት ዶ/ር ቢንያም አስራት በአካባቢው የተከሰተውና “የሔሞሬጂክ ፊቨር” እንደሆነ በተገመተው እና በኋላ ላይ ማርበርግ ቫይረስ (marburg virus) መሆኑ የተረጋገጠው ተላላፊ በሽታ ሳቢያ ስድስት ሰዎች መሞታቸውን ለአንድ ዓለም አቀፍ ሚዲያ ይፋ ማድረጋቸውን ተከትሎ ከሓላፊነታቸው መነሳታቸው ተገልጿል።
ባለሙያው ከሆስፒታሉ ሥራ አስኪያጅ ምስጢሩ ሐምደኪ በተጻፈ ደብዳቤ ከሕዳር 5 ቀን ጀምሮ ከሓላፊነት መነሳታቸው የተነገራቸው ሲሆን፣ ዶ/ር ቢንያም ከሓላፊነት ከተነሱ በኋላ የሆስፒታሉን ቅጥር ግቢ እንዳይገቡ መከልከላቸው የተረጋገጠ ሲሆን፣ ይህ ደግሞ ለሕዝብ እውነትን የተናገረን ባለሙያ ለመቅጣት የተደረገ መሆኑን የስራ ባልደረቦቹ ለሆርን ፍሪኩዌንሲ ገልጸዋል።
ሆስፒታሉን በበላይነት የሚያስተዳድረው የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ጤና ቢሮ በጉዳዩ ላይ ምንም ዓይነት አስተያየት ለመስጠት ፍቃደኛ አልሆነም።











