Home / ፖለቲካ / ‹‹ምርጫውን ለማካሄድ በአስቻይ ሁኔታ ላይ መግባባት ሳይደረስ የእጩዎች ምዝገባ ጥሪ ተገቢ አይደለም›› የፖለቲካ ፓርቲዎች

‹‹ምርጫውን ለማካሄድ በአስቻይ ሁኔታ ላይ መግባባት ሳይደረስ የእጩዎች ምዝገባ ጥሪ ተገቢ አይደለም›› የፖለቲካ ፓርቲዎች

የምርጫ ቦርድ ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የሚወዳደሩ እጩዎች ምዝገባ ጥሪ ማቅረቡን ተከትሎ የፖለቲካ ፓርቲዎች በመጀመሪያ ደረጃ ምርጫውን ለማካሄድ አስቻይ ሁኔታ ለመኖሩ መግባባት ላይ ሳይደረስ ይህ አይነት ጥሪ መደረጉ ተገቢነት የለውም ሲሉ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል፡፡

ሆርን ፍሪኩዌንሲ ያነጋገራቸው የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች እና አባላት እንደተናገሩት በአገር ውስጥ ያለው የጸጥታ ሁኔታን በትኩረት አንስተው እንዲሁም የምርጫው የጊዜ ሰሌዳውንም በሚመለከት ጉዳዩ በግልጽ ለውይይት ባልቀረበበት ወቅት ከምርጫ ቦርድ እጩዎችን እንድናስመዘግብ መደረጉ ተቀባይነት የለውም ብለዋል፡፡

ምርጫ ቦርድ በተያዘው ዓመት አካሄደዋለሁ ለለው ምርጫ ፓርቲዎች ዕጩዎችን እንዲያስመዘግቡ ያሳሰበው በአጭር የጊዜ ገደብ ውስጥ ነው፡፡ ቦርዱ በወጣው ማስታወቂያ መሰረት ሁሉም ፓርቲዎች እጩዎቻቸውን ከዛሬ ህዳር 8 እስከ ህዳር 23/2018 ዓ.ም ድረስ ማስመዝገብ ይጠበቅባቸዋል።

ይሁን እንጂ ቦርዱ ያቀረበውን የእጩዎች ምዝገባ ጊዜ ገደብ እንደማይቀበሉት ሆርን ፍሪኩዌንስ ያነጋገራቸው የፓርቲ አመራሮች ገልጸዋል። ቦርዱ ለውይይት ያቀረበው የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ የጋራ መግባባት ላይ ሳይደረስበት፣ የእጩዎች ምዝገባ አካሂዳለሁ ማለተለ አግባብነት የለውም ተብሏል።

ምርጫ ቦርድ የቀረበለትን አስቻይ ሁኔታ የመፍጠር ጉዳይ ላይ ቅድሚያ ሰጥቶ መሥራት ካልቻለ፣ ከፓርቲዎች ጋር ተግባብቶ የመቀጠሉ ጉዳይ አጠያያቂ መሆኑንም አመራሮች ጠቁመዋል።

በመንግሥት እና በምርጫ ቦርድ ደረጃ በተያዘው ዓመት ይካሄዳል የተባለው ምርጫ ላይ በርካታ ፓርቲዎች ከወዲሁ ጥያቄ እያነሱ ነው። ፓርቲዎች ያለ ልዩነት የጋራ አቋም ያደረጉት ነጻ ምርጫ ለማካሄድ በተለያዩ አካባቢዎች የቀጠሉ የእርስ በእርስ ግጭት ጦርነቶች ይቁሙ የሚል ነው። አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ የተሟላ ምርጫ ማካሄድ የሚያስችል የሰላምና ጸጥታ ሁኔታ አለመኖሩን ፓርቲዎች ባወጧቸው የጋራ መግለጫዎች ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ)፣ እናት ፓርቲ፣ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ)፣ አንድ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አኢዴፓ) እና አማራ ግዮናዊ ንቅናቄ (አግን) ህዳር 8/2018 ባወጡት የጋራ መግለጫ፣ የእርስ በእርስ ግጭትና ጦርነት ቆሞ ለምርጫ አስቻይ ሁኔታ መፈጠር አለበት በማለት ቅደመ ሁኔታ አስቀምጠዋል።

የእርስ በእርስ ጦርነት መቆምን እንደ ቅድመ ሁኔታ ያስቀመጡት ፓርቲዎቹ፣ የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ወደ ተግባር ከመሸጋገሩ ቀደም ብሎ በተግባር የተረጋገጠ እርምጃ በመውሰድ አለበት ብለዋል፡

በተመሳሳይ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ፣ የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢሶዴፓ)፣ ባልደራስ፣ ኅብር ኢትዮጵያና ዓረና ያሉ ፓርቲዎችም፣ ለቀጣዩ ምርጫ የጋራ ቅድመ ሁኔታ አቅርበዋል፡፡ ፓርቲዎቹ ያስቀመጧቸው ቅድመ ሁኔታዎች በሁሉም አካባቢዎች ግጭትና ጦርቶች በአስቸኳይ መቆምና የፖለቲካ እስረኞች ያለ ቅድመ ሁኔታ መፍታት ቀዳሚዎቹ ናቸው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *