ዓለም አቀፍ የቀይ መስቀል ኮሚቴ በፋኖ ኃይሎች የተማረኩ የመንግሥት ተዋጊዎችን መጎብኘቱን አስታውቋል።
ኮሚቴው ከሁለት ሳምንት ገደማ በፊት በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ የተከሰትውን ውጊያ ተከትሎ፣ በፋኖ ኃይሎች ለተማረኩ የመንግሥት ተዋጊዎች ሰብዓዊ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገልጿል።
የፋኖ ኃይሎች በመቶዎች የሚቆጠሩ የመከላከያ ሠራዊት አባላትን እንደማረኩ በመግለጽ፣ ቀይ መስቀል ሰብዓዊ ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል።
የዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ኮሚቴ ጥሪውን ተቀብሎ ለምርኮኞቹ ሰብአዊ ድጋፎ እያቀረበ መሆኑን በጉዳዩ ላይ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
ኮሚቴው ከአንድ ሳምንት ወዲህ የባለሙያዎች ቡድን ወደ አካባቢው ልኮ በላሊበላና በወልዲያ እንዲሁም በአካባቢው ላሉ ስድስት የጤና ተቋማት የድንገተኛ ሕክምና እርዳታ መስጫ ቁሳቁስ ማቅረቡን ገልጿል።
በውጊያው ከባድ ጉዳት ለደረሰባቸው 250 ሰዎች የቀዶ ጥገና እና የሕክምና እርዳታ ለመስጠት የሚበቃ ድጋፍን ያካተተ ነው ተብሏል። እንዲሁም አስቸኳይ የቀዶ ጥገና ሕክምና የሚያስፈልጋቸው 16 ከባድ ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች ወደ ሕክምና ተቋማት ማድረሱን ኮሚቴው አስታውቋል።
ኮሚቴው ከድጋፉ በተጨማሪ እስረኞችን በመጎብኘት ያሉበትን ሁኔታ የተመለከትን ሲሆን ከቤተሰቦቻቸው ጋር መገናኘት እንዲችሉ እገዛ ማድረጉንም ገልጿል። “በግጭቱ በጣም የተጎዱ ማህበረሰቦች መዘንጋት የለባቸውም። ብዙ ሰዎች ወደ ጤና አገልግሎት፣ ወደ ገበያ እና ወደ እርሻ ቦታቸው መሄድ አልቻሉም” ሲሉ በላሊበላ የዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ኮሚቴ የመስክ ቡድን መሪ ማርቲን ታልማን ተናግረዋል። ማርቲን አያይዘውም በተለይም ደግሞ በኩል መስክ እና ሙጃ አካባቢዎች በተፈጠረው ውጊያ በርካቶች መገደላቸውን እና መቁሰላቸውን አያይዘው ጠቁመዋል፡፡
ዓለም አቀፍ የቀይ መስቀል ኮሚቴ የሕክምና እርዳታ ማድረሱን አሁንም መቀጠሉን ገልጿል። ኮሚቴው ከሁሉም የግጭቱ ተሳታፊ ወገኖች ጋር በመገናኘት ሲቪል ሰዎች እና እስረኞች በዓለም አቀፍ የሰብአዊነት ሕግ መሰረት ከለላ ማግኘታቸውን ለማረጋገጥ እንደሚሰራ ጠቁሟል።










