ባህላችንን እንዳናሳይ ተደርገናል ሲሉም ተሳታፊዎች ተናግረዋል
የኢትዮጵያን ባህል ለተለያዩ የብሪክስ አባል አገራት በማቅረብ ላይ የሚገኘው ኪን-ኢትዮጵያ መድረክ ከአርቲስቶች ጉቦ በመቀበል ክስ ቀረበበት።
በቅርቡ የኢትዮጵያን ባህል በማስተዋወቅ የልዑካን ቡድኑን ይዞ ከቻይና እስከ ሩሲያ ሲጓዝ የነበረው ኪን ኢትዮጵያ የተሰኘው የባህል ጉዞ፤ በልዑካን ቡድኑ ውስጥ ለመካተት አርቲስቶች እስከ 80 ሺ ብር እንዲከፍሉ መጠየቃቸው ታውቋል፡፡
የኪን-ኢትዮጵያን የባህል ጉዞን ለማዘጋጀት በሙዚቃ አቀናባሪ ካሙዙ ካሳ ባለቤትነት የሚመራው ሻኩራ ፕሮዳክሽን ከባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ጋር ስምምነት በመፈራረም ስራውን ሲከውን መቆየቱን ለማወቅ ተችሏል። ይሁን እንጂ በዚህ የባህል ጉዞ ላይ ከቻይና መልስ በሩሲያው የባህል ዝግጅት ላይ እንዳይሳተፉ ተቆርጠው የቀሩ ድምጻውያን በይፋ ቅሬታ አቅርበዋል። ወደ ሩሲያ ተጉዘው በባህል ዝግጅቱ ላይ እንዳይሳተፉ ተከልክለናል ያሉ ድምጻዊያን እሰከ 80 ሺህ ብር ተጠይቀናል ብለዋል። ወደ ሩሲያ እንዳይጓዙ ከተቀነሱ የኪን-ኢትዮጵያ አባላት መካከል ድምጻዊ ምትኩ በቀለ ደረሰብኝ ያለውን በደል ተናግሯል። ድምጻዊ ምትኩ ወደ ሩሲያ ለመጓዝ ከካሙዙ ካሳ ጋር የዝግጅቱ አስተባባሪ ከሆነው ወንድዬ አበበ (ወንዴ ኮንታ) 80 ሺህ ብር እንዲከፍል ተጠይቆ መክፈል ባለመቻሉ መቀነሱን በጉዳዩ ላይ በማኅበራዊ ሚዲያ ባሰራጨው ቪዲዮ ላይ ተናግሯል።
ከዚህም በተጨማሪ የኪን ኢትዮጵያ የባህል ጉዞ የአማራ ባህል በአግባቡ እና በቻይናው መድረክ እንደታየው በሩሲያ እንዳይታይ በልዑካን ቡድኑ መሪዎች ጫና እንደተደረገበት እና ይህንንም ተከትሎ በሩሲያ የሚገኙ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ አባላት ከፍተኛ ቅሬታ ማሰማታቸው ሆርን ፍሪኩዌንሲ ተረድቷል፡፡
ምክንያቱ በውል ባልታወቀ ሁኔታ የአማራ ባህል ከሌሎች ባህሎች እኩል እንዳይቀርብ መደረጉ ቅሬታ ያደረባቸው በሩሲያ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ለምን የአማራ ባህል ተለይቶ ከመድኩ ተገደበ የሚል ጥያቄ አንስተው የነበረ ቢሆንም የተሰጠው ምላሽ አሉታዊ መሆኑ ተገልጿል።
በጉዳዩ ላይ የባህል እና ስፖርት ሚንስቴር ሚንስትር ዲኤታ ነብዩ ባዬን ማብራሪያ እንዲሰጡ ሆርን ፍሪኩዌንሲ ጥያቄ ያቀረበላቸው ሲሆን ሚንስትር ዲኤታው ጉዳዩን እንደማውቁት እና ለመስሪያ ቤታቸውም የቀረበ ምንም አይነት ቅሬታ አለመኖሩን አሰታውቀዋል፡፡ በተጨማሪም ከመንግስት ወገን የልዑካን ቡድኑን በመምራት በሩሲያ የተገኙት በሚንስቴር መስሪያ ቤቱ የባህልና ቋንቋ ልማት ዘርፍ ሚንሰትር ዲኤታ ነፊሳ አልማህዲ ከሆርን ፍሪኩዌንሲ ለቀረበላቸው ጥያቄ ማብራሪያ ከመስጠት ተቆጥበው በደብዳቤ ጥያቄያችንን እንድናስገባ የመከሩ ሲሆን በአጭሩ ግን የተናፈሰው ወሬ ሁሉ ትክክል ነው ማለት አይደለም የሚልም ምላሽ አክለዋል፡፡











