Home / ፖለቲካ / በአበርገሌ ወረዳ በመድፍ ቁምቡላ ፍንዳታ የሰዎች ሕይወት አለፈ

በአበርገሌ ወረዳ በመድፍ ቁምቡላ ፍንዳታ የሰዎች ሕይወት አለፈ

በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር በአበርገሌ ወረዳ 03 ቀበሌ በበልታርፍ ጎጥ በቤት ውስጥ በተከሰተ የመድፍ ቁምቡላ ፍንዳታ የአምስት ሰዎች ሕይወት ማለፉን የወረዳው ፖሊስ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።

የወረዳው ፖሊስ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ኢንስፔክተር መንግስቴ ደባሽ ለሆርን ፍሪኩዮንሲ በላኩት መረጃ ላይ እንደገለጹት፣ አደጋው የተከሰተው በቤት ውስጥ የነበረን የመድፍ ቁምቡላ ለመውቀጫነት ለማዋል ሲቀጠቅጡት በመፈንዳቱ ነው። በዚህም ምክንያት የአምስት ሰዎች ሕይወት ወዲያውኑ ያለፈ ሲሆን፣ በሁለት ሰዎች ላይ ደግሞ ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል ብለዋል።ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖች በአሁኑ ወቅት የረ_አቚ በተሰኘ ጤና ጣቢያ የሕክምና እርዳታ እየተደረገላቸው እንደሚገኝ ተገልጿል።

ከሰው ሕይወት በተጨማሪ በእንስሳት እና በንብረት ላይ ከፍተኛ ውድመት መድረሱን የገለጹት ሃላፊው፤ ፖሊስ ስለ አደጋው ሙሉ መረጃ ለማግኘት በአሁኑ ወቅት ተጨማሪ ምርመራ እያደረገ እንደሚገኝ ተመላክቷል።

ይህ በአበርገሌ ወረዳ የደረሰው አሳዛኝ ክስተት፣ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ጦርነት ወቅት በአካባቢው ተበትነው የቀሩና ሳይፈነዱ የወደቁ የጦር መሣሪያ ቅሪቶች አሁንም ድረስ በንጹሐን ዜጎች ሕይወት ላይ ጉዳት እያደረሱ መሆኑን የሚያሳይ ነው ተብሏል። ጦርነቱ ካበቃ በኋላም እንዲህ ያሉ የጦር መሣሪያ ቅሪቶች በተለያዩ አካባቢዎች ለሰዎች ሞትና አካል ጉዳት ምክንያት እየሆኑ እንደሆነ ተመላክቷል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *