Home / ፖለቲካ / በራያ አላማጣ የሕወሃት ኃይሎች የቤተክርስቲያን አገልጋዮችን አፍነው እየወሰዱና ማሕተም እየነጠቁ ነው ተባለ

በራያ አላማጣ የሕወሃት ኃይሎች የቤተክርስቲያን አገልጋዮችን አፍነው እየወሰዱና ማሕተም እየነጠቁ ነው ተባለ

የሕወሃት ኃይሎች በራያ አላማጣ ከተማና አካባቢው እየፈጸሙት ያለው የሰብአዊ መብት ጥሰትና የነዋሪዎችን ሰቆቃ ያባባሰ ድርጊት በዚህ ሳምንት ተጠናክሮ መቀጠሉን የከተማዋ ከንቲባ አቶ ሃይሉ አዱኛ ገለጹ።

ከንቲባው ለሆርን ፍሪኩዮንሲ በሰጡት ቃል፣ የሕወሃት ታጣቂዎች ከዘረፋና ከአፈና ባሻገር፣ የሕዝቡን ልብ በእጅጉ የሚነካ የሃይማኖትና የማንነት ጭቆና እየፈጸሙ መሆኑን አስረድተው፤ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችን አፍነው በመውሰድም በግዴታ ማሕተም እየነጠቁ እንደሚገኙም ታውቋል። በከንቲባው ገለጻ መሰረት፣ የሕወሃት ኃይሎች በከተማዋ በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ላይ ቀጥተኛ ጣልቃ ገብነት በማድረግ፣ አገልጋዮቹ “በአማርኛ ቋንቋ እንዳትቀድሱ” የሚል አስገዳጅ ትዕዛዝ የተላለፈ ሲሆን፣ ሁሉም ሃይማኖታዊ ሥርዓተ አምልኮዎች በትግረኛ ቋንቋ ብቻ እንዲከናወኑ ማስገደድ መጀመሩን ለማወቅ ተችሏል። ከዚህም ጋር ተያይዞ በአማረኛ ጽሑፍ የተቀረጸባቸውን የቤተክርስቲያናቱን ማዕተሞች በኃይል በመንጠቅ፣ በምትኩ በትግረኛ ቋንቋ ጽሑፍ የተቀረጸባቸውን ማሕተሞች እንዲጠቀሙ ማስገደዳቸው ነው ብለዋል።

ይህ ድርጊት በአካባቢው አማኞችን ሃይማኖታዊ መብት የሚጥስ እና ከማንነት ጋር የተቆራኘ ስነልቦናዊ ጫና የሚፈጥር ተግባር መሆኑን አቶ ሃይሉ አብራርተዋል። ታጣቂዎቹ በከተማዋ ነዋሪዎች ላይ የሚፈጽሙት አፈናና ብዝበዛ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል ያሉት ከንቲባው፤ ነዋሪዎችን አግተው በመውሰድ ገንዘብ እየተቀበሉ የሚለቁ ሲሆን፣ ይህም የብዙ ቤተሰቦችን ኢኮኖሚያዊ መሰረት አናግቷል ብለዋል።

ከዚህም የከፋው ጫና ደግሞ፣ ነዋሪዎች የራሳቸውን ህጋዊ መታወቂያ እንዲጥሉና የትግራይ ክልልን የሚገልጽ መታወቂያ ብቻ እንዲይዙ መገደዳቸው ነው ብለዋል። ከንቲባው ይህ ድርጊት በአካባቢው ሕዝብ የማንነት ጥያቄ ላይ የፖለቲካዊ ቁጥጥርና ጫና ለማድረግ ያለመ ሲሆን፣ ነዋሪዎችም በአስገዳጅ ሁኔታ ለከፋ የማንነት ቀውስ እየተዳረጉ መሆኑን አስረድተዋል። በራያ አላማጣ ገጠራማ አካባቢዎች የሚኖሩ አርሶ አደሮችም ከአፈናውና ከሃይማኖት ጫናው ባልተናነሰ መልኩ በኢኮኖሚያዊ ጥቃት እየተሰቃዩ ነው ብለዋል ከንቲባው።

በሕወሃት ኃይሎች ተዘርግቷል የተባለለት የዘረፋ ሰንሰለት፣ አርሶ አደሮቹ ለአመታት የደከሙበትንና የደረሰውን ሰብላቸውን አሳጥቷቸዋል። በተለይም ማሽላና በቆሎን የመሳሰሉ ጠቃሚ ሰብሎች፣ ከእርሻው ላይ እየተቆረጡ፣ በኩንታል እየተጫኑና እየተወሰዱ ነው ብለዋል። ታጣቂዎቹ ሰብሉን በመንገድ ላይ ሳይቀር እየጠበሱ በመመገብ የገበሬውን የአመት ሙሉ የጉልበት ውጤት በአይናቸው ፊት በማባከን ላይ ናቸው ብለዋል። ይህ ድርጊት ገበሬውን በአስቸኳይ ለረሃብና ለከፋ የምግብ ዋስትና እጦት የሚዳርግ አደገኛ ድርጊት መሆኑን ከንቲባው ገልጸዋል።

በመጨረሻም፣ አቶ ሃይሉ አዱኛ እነዚህ ሁሉ አሰቃቂ ድርጊቶች በዚህ ሳምንት ተባብሰው መቀጠላቸውን በመግለጽ፣ በአካባቢው ያሉ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ቢኖሩም፣ ይህንን የሕወሃት ታጣቂዎች የዘረፋና የማፈን ሰንሰለት ሊያስቆሙት እንዳልቻሉ አስረድተዋል። በጉዳዩ ላይ ከሕወሓት ወገን ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም፡፡

Sign Up For Daily Newsletter

Stay updated with our weekly newsletter. Subscribe now to never miss an update!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *