Home / ፖለቲካ / በጋምቤላ በታጠቁ አካላት በተፈጸመ ጥቃት ውጥረት ተፈጥሯል

በጋምቤላ በታጠቁ አካላት በተፈጸመ ጥቃት ውጥረት ተፈጥሯል

በጋምቤላ ከተማ ውስጥ ከሰሞኑ በታጠቁና የፖሊስ ልብስ በለበሱ አካላት የሽብር ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ አዲስ ግጭት እንዳይቀስ በሚል ከባድ ስጋት ተፈጥሯል፡፡

በጋምቤላ ከተማ ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች እንደገለጹት፣ የተደራጁ ናቸው የተባሉ እና የታጠቁ አካላት የክልሉን ፖሊስ ልብስ ለብሰው በመኪና ሲንቀሳቀሱ በነበሩ ነዋሪዎች ላይ የጥይት እሩምታ በመክፈት ጥቃት ማድረሳቸውን ለሆርን ፍሪኩዌንሲ አስታውቀዋል። በዚህ ጥቃት ሁለት ሰዎች ሕይወታቸው ወዲያውኑ ሲያልፍ፤ በርካቶችም የመቁሰል አደጋ ደርሶባቸዋል። ጥቃቱን ፈጽመው የተሰወሩት አካላት እስካሁን ድረስ በቁጥጥር ሥር አለመዋላቸው ታውቋል።

በክልሉ ቀደም ሲል በተደጋጋሚ ግጭቶች ሲከሰቱ የነበሩ ሲሆን፣ በግጭቶቹም በርካታ ሰዎች ለሞትና ለአካል ጉዳት መዳረጋቸው ይታወሳል። ይህ አዲስ ጥቃት ከተፈጸመ በኋላም፣ የጋምቤላ ከተማ አጠቃላይ እንቅስቃሴ መቀዛቀዝ ታይቶበታል፤ ነዋሪዎቹም ከፍተኛ ፍርሀት ውስጥ መሆናቸውን ለሆርን ፍሪኩዮንሲ ገልጸዋል። በተፈጠረው ችግርም ከዚህ ቀደም በክልሉ ውስጥ የበሔር መልክ ያለው ግጭት ዳግም አገርሽቶ ተጨማሪ የሰላም ቀውስ ውስጥ እንዳይግቡ ነዋሪዎች ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡

የነዋሪዎቹን ስጋት ተከትሎ፣ የጋምቤላ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጋሕዴን) ሊቀመንበር አቶ ሳይመን ቱት ስለጉዳዩ ተጠይቀው ምላሽ ሰጥተዋል።

አቶ ሳይመን ቱት እንደተናገሩት፣ በክልሉ ከሰሞኑ የታጠቁ ኃይሎች በመኪና ተሳፍረው በሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች ላይ ተኩስ መክፈታቸውን አረጋግጠዋል። በተከፈተው የጥይት ተኩስም ከሁለት በላይ ሰዎች መሞታቸውንና በርካቶች መቁሰላቸውን ገልጸዋል።

ሊቀመንበሩ አክለውም፣ “ድርጊቱ በሁለቱ ብሔረሰቦች መካከል ጋብ ብሎ የቆየውን ግጭት ድጋሚ ለመቀስቀስ ታስቦበት የተፈጸመ የሽብር ጥቃት ነው” ሲሉ ተናግረዋል። ከዚህ የሽብር ጥቃት እና ከነዋሪዎች ከፍተኛ የስጋት ስሜት ጋር ተያይዞ የክልሉን ኮሙኒኬሽን ቢሮና የጸጥታ ዘርፍ ቢሮን ለማነጋገር ተደጋጋሚ የስልክ ሙከራ ቢደረግም፣ የስልክ ጥሪ ባለማንሳታቸው ምክንያት ምላሽ ማግኘት አልተቻለም።

የክልሉን ፖሊስ ልብስ ለብሰው ጥቃት ፈጽመዋል የተባሉት አካላት ማንነትና ዓላማ፣ እንዲሁም የክልሉ መንግሥት በሰላም ላይ የተደቀነውን አደጋ ለመከላከል ምን ዓይነት የጸጥታ እርምጃዎችን እንደሚወስድ ለማወቅ የሚደረገው ጥረት ቀጥሏል።

በጋምቤላ ከዚህ ቀደም በኑዌር እና አኝዋክ ብሔረሰቦች መካከል የብሔር መልክ እንዲይዝ ተደርገው የሚቀሰቀሱ ግጭቶች መኖራቸው የሚታወስ ሲሆን በተለይም ደግሞ በክልሉ ተጠልለው ከሚገኙ የጎረቤት አገር ደቡብ ሱዳን ዜጎች መጨመር፣ የመሬት እና የፖለቲካ ነክ ጉዳዮች ዋነኛ መነሻዎች መሆናቸው ሲጠቀስ ቆይቷል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *