Home / ፖለቲካ / ከጌታቸው ረዳ ጋር ወደ አዲስ አበባ የተጓዙት ባለሥልጣናት ሹመት ቀጥሏል

ከጌታቸው ረዳ ጋር ወደ አዲስ አበባ የተጓዙት ባለሥልጣናት ሹመት ቀጥሏል

የቀድሞው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ጌታቸው ረዳን ተከትለው፣ ከመቀሌ ወደ አዲስ አበባ የኮበለሉ የቀድሞ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ባለሥልጣናት በፌደራል መንግሥት ሹመት መሰጠቱ እንደቀጠለ መሆኑ ተሰምቷል።

በፌዴራል መንግሥት የተሾሙት የቀድሞው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮች ናቸው። ከተሿሚዎቹ መካከል የትግራይ የምግብ፣ መድኃኒትና ጤና ተቋማት ቁጥጥር ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር የነበሩት ጣዕመ አረዶም ይገኙበታል። ጣዕመ የኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክር ሆነው በጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ መሾማቸውን ሆርን ፍሪኩዌንሲ ከሹመት ደብዳቤያቸው ተረድቷል።

በተመሳሳይ የህወሓት ከፍተኛ አመራር የነበሩት ሺሻይ አማረ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ ትምህርትና ሥልጠና ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሆነው ተሾመዋል።

ከዚህ ቀደም በጊዜያዊ አስተዳደሩ ወስጥ በከፍተኛ አመራር የነበሩት ክንደያ ገብረህይወት (ፕ/ር) በሚኒስትር ድኤታ ደረጃ የትምህርት ሚኒስትር አማካሪ ነው መሾማቸው ይታወሳል።

ደጋፊ የካቢኔ አባላቶቻቸውን አስከትለው ወደ አዲስ አበባ የሸሹት ጌታቸው ረዳ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ሆነው መሾማቸው የሚታወስ ሲሆን፤ ከጌታቸው ረዳ ጋር ወደ አዲስ አበባ ሸሽተው የነበሩ የቀድሞ የጊዜያዊ አስተዳደሩ አመራሮች ካለፈው ሰኔ 2017 ዓ.ም ጀምሮ ደሞዛቸው እንዲታገድ ሆኗል፡፡ ጌታቸውን የተኩት የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት ሌተናል ጀነራል ታደሰ ወረደ አዲስ አበባ የከተሙ አመራሮቸን ደመወዝ ያገደበትን ደብዳቤ ሆርን ፍሪኩዌንሲ ተመልክቷል።

ሕጋዊ የፖለቲካ ሰውነቱን በምርጫ ቦርድ ባጣው በደብረፅዮን ገ/ሚካኤል የሚመራው የህወሓት ቡድን ጋር በመጋጨት የፖለቲካ መካረር ውስጥ የሚገኘው የጌታቸው ቡድን ፓርቲ መመስረቱ ይታወሳል። ከዚህም ጋር ተያይዞ በጌታቸው ረዳ የሚመራው ቡድን ዴሞክራሲያዊ ስምረት ትግራይ (ስምረት) ከምርጫ ቦርድ የቅድመ ምዝገባ ፈቃድ አግኝቶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑ ይታወቃል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ በፌዴራል ተቋማት ሹመት የሰጧቸው የህወሓት ተገንጣይ አመራሮች የስምረት ፓርቲ መሥራቾች ናቸው። በጌታቸው ረዳ የሚመራው እና አዲስ የተቋቋመው ፓርቲ ህወሓትን ለመታገል ከፌደራሉ መንግሥት ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን ባወጣቸው መግለጫዎች አመላክቷል።

Sign Up For Daily Newsletter

Stay updated with our weekly newsletter. Subscribe now to never miss an update!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *