ከአዲስ አበባ ወደ አማራ ክልል ምስራቅ ጎጃም ዞን ዋና መቀመጫ ደብረማርቆስ ከተማ በየብስ ትራንስፖርት በመጓዝ ላይ የነበሩ 40 ገደማ ሰዎች፣ኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ወረ ጃርሶ ወረዳ ልዩ ስሙ አሊዶሮ በሚባል ቦታ ላይ መታገታቸውን ሆርን ፍሪኩዌንሲ አረጋግጧል።
እገታው የተፈጸመው ታህሳስ 27/2018 በቀን ሲሆን፣ እገታው ሲፈጸም መንገደኞችን የጸጥታ ድጋፍ በማድረግ በማጀብ ላይ የተሰማሩ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በቅርብ ርቀት ላይ ነበሩ ተብሏ። የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ታጋቾች ሲጓዙበት ከነበረ ኤፍ ኤም ባስ በቅርብ ርቀት ከፊት እና ኋላ እንደነበሩ አንድ በዚያው መስመር ያለፉ መንገደኛ ለዝግጅት ክፍላችን ተናግረዋል።
ከ40 በላይ ተጓዦችን የያዘው ወደ ደብረማርቆስ የሚያቀና ኤፍ ኤም ባስ ላይ ታጣቂዎች በድንገት የተኩስ እሩምታ ከፍተው ካስቆሙ በኋላ ሁሉንም ተሳፋሪዎች ወደ ጫካ አግተው ሲወስዷቸው በአቅራቢያ የነበሩ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች፣ ከተወሰነ የተኩስ ልውውጥ ውጭ ታጣቂዎቹን ተከትለው ታጋቾቹን ማስለቀቅ አለመቻላቸውን ምንጮች ጠቁመዋል።
እንደ ደብረ ማርቆስ ነዋሪዎች ገለጻ በተሽከርካሪው ውስጥ የነበሩት መንገደኞች አብዛኞቹ የደንበጫ፣ የአማኑኤል፣ የደብረ ኤልያስ እና የጅጋ አካባቢ ተወላጆች ናቸው። ከታጋቾቹ መካከል አንዱ በያዘው ስልክ አማካኝነት “በሸኔ ታጣቂዎች ታግተን እየተወሰድን ነው” የሚል አስቸኳይ መልዕክት ለቤተሰቦቹ መላክ የቻለ ቢሆንም ከዚያ በኋላ ግን ስልኮች መዘጋታቸው ታውቋል።
ተሳፋሪዎች የታገቱበት የሕዝብ ማመላለሻ ብዙ ቦታ በጥይት ተመትቶ ባዶውን መንገድ ቆሞዳር መመልከታቸውን እገታው ከተፈጸመበት አውቶብስ ኋላ በሌላ ተሽከርካሪዎች ሲጓዙ የነበሩ የዓይን እማኞች ለሆርን ፍሪኩዌንሲ ተናግረዋል። ታጣቂዎች እገታውን ለመፈጸም በከፈቱት የተኩስ እሩምታ የተገደሉና የቆሰሉ ሰዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ የተገለጸ ቢሆንም፣ በተጨባጭ የደረሰውን ጉዳት ማረጋገጥ አልተቻለም።
የአዲስ አበባ ጎጃም መስመር ለዓመታት በተደጋጋሚ እገታ የተፈጸመበት መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን ከወራት በፊት በተከታታይ ሳምንታት ከ100 በላይ ሰዎች በዚሁ ቦታ በተመሳሳይ ሁኔታ ታግተው እንደነበር ይታወሳል።
በተደጋጋሚ እገታ በሚፈጸምበት ቦታ ላይ መንግሥት ጠንካራ ጥበቃ እንዲያደርግ በተደጋጋሚ ጥሪ ቢቀርብለትም፣ የዜጎችን በነጻነት የመንቀሳቀስ መብትና ደህንነት አላስከበረም በሚል ቅሬታ ሲቀርብም ቆይቷል። በተጨማሪም መንግስት ችግሩ ከተከሰተ በኋላ አፋጣኝ ምላሽ እና መፍትሔ ለመስጠትም ሲንቀሳቀሱ ከመንግስት ወገን እንደማይታይ ከዚህ ቀደም የተጎጂ ቤተሰቦች መናገራቸው ይታወሳል።












