በጋምቤላ ክልል መዲና እና አካባቢው የተከሰተውን የፀጥታ ችግር ተከትሎ ከተማዋን ወደ መደበኛ እንቅስቃሴዋ ለመመለስ እና ሰላምን ለማስፈን ወደ ተለያዩ አካባቢዎች ተሰማርተው በነበሩ የመንግስት የፀጥታ ኃይሎች ላይ፣ ዛሬ ከሰዓት በኋላ በታጣቂዎች ድንገተኛ ተኩስ ተከፍቶባቸዋል።
ጥቃቱ የተፈጸመው “ባሮ ማዶ”ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ሲሆን፣ የታጠቁ የአኙዋክ ሚሊሻዎች ወታደራዊ ትጥቅ ይዘው ሲንቀሳቀሱ መታየታቸውን ተከትሎ የፌዴራል ፖሊስ እና የሀገር መከላከያ ሰራዊትን ያቀፈው የጋራ ግብረ ኃይል ትጥቅ ለማስፈታት እርምጃ ለመውሰድ ሲሞክር ግጭቱ ተቀስቅሷል ሲሉ ነዋሪዎች ለሆርን ፍሪኩዮንሲ ገልጸዋል።
በዚህ ድንገተኛ ጥቃት ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ የፀጥታ አካላት በጥይት ተመትተው ጉዳት ደርሶባቸዋል ተብሏል። ይሁን እንጂ ታጣቂዎች ናቸው ከተባሉት ወገን ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው የጸጥታ ኃይላት የአኝዋክ ወጣቶችን በመምረጥ ለማሰር እና ራሳቸውን እንዳይከላከሉ እያደረጉ በነበረበት ወቅት ከወጣቶች ጋር አለመግባባት ተፈጠረ እንጂ የከፋ ነገር አልተፈጠረም ሲሉ የተፈጠረውን ኹነት አስተባብለዋል፡፡
በሰነበተው ግጭት ምክንያት የተጣለው የሰዓት እላፊ ገደብ እና የተቋማት በከፊል መዘጋት በከተማዋ ነዋሪዎች ላይ ከፍተኛ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጫና እያሳደረ ይገኛል። የንግድ ቤቶች፣ ባንኮች እና ገበያዎች በከፊል ተዘግተው በመቆየታቸው ነዋሪዎች መሠረታዊ ፍጆታዎችን ለማግኘት በእጅጉ መቸገራቸውን ገልጸዋል። በተለይም በዕለት ስራ ኑሯቸውን የሚመሩ የከተማዋ ነዋሪዎች ለከፍተኛ የምግብ እና የገቢ እጥረት መጋለጣቸው የታወቀ ሲሆን፣ የመንግስት መስሪያ ቤቶችም በከፊል አገልግሎት ባለመስጠታቸው የህዝብ አገልግሎት ጉዳዮች ተቋርጠው ይገኛሉ።
በከተማዋ የተጣለው የእንቅስቃሴ ገደብ የውስጥ ለውስጥ ትራንስፖርትን ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ያገደ ሲሆን፣ ይህም የህመምተኞችን እና የአረጋውያንን እንቅስቃሴ አዳጋች አድርጎታል ሲሉ የሆርን ፍሪኩዮንሲ ምንጮች ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት በጋምቤላ ከተማ ዋና ዋና መንገዶች ላይ የመንግስት የፀጥታ ኃይሎች በብዛት የሚታዩ ሲሆን፣ ሁኔታው አሁንም በከፍተኛ ውጥረት ውስጥ እንደቀጠለ ነው። ክልላዊ መንግስቱም ሆነ የፌዴራል ፀጥታ አካላት ስለዛሬው ጥቃት እና ስለሚቀጥለው የእንቅስቃሴ ገደብ እስካሁን በይፋ የሰጡት መግለጫ የለም።












