የጋምቤላ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የፖሊስ ኮሚሽነር ኡጉላ ኡጁሉ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ምንጮች ለሆርን ፍሪኩዌንሲ ገለጹ፡፡
ኮሚሽነሩ በሕግ ቁጥጥር ስር መዋላቸው ይነገር እንጂ አሁንም ድረስ ያሉበት ስፍራ እንደማይታወቅ ምንጮች ጨምረው ገልጸዋል፡፡
በክልሉ በተከሰተው የሰላም መደፍረስ ጋር በተያያዘ ምክንያት በቁጥጥር ስር ሳይውሉ እንዳልቀረው የተገመቱት ኡሞድ ኡጁሉ፤ በፌደራል የጸጥታ ኃይላት፤ በፌደራል ፖሊስ እና መከላከያ አባላት ተይዘው መወሰዳቸውን እና የደረሱበትም እንደማይታወቅ ታውቋል፡፡ የደፈረሰው የሰላም እጦት በማንነት ላይ ያነጣጠረ መሆኑ እና በርካቶችን ለሕልፈት እና ከቤት ንብረት ማፈናቀሉ የሚታወስ ሲሆን የጋምቤላ ከተማ የፖሊስ አዛዥ መገደላቸውም የሚታወስ ነው፡፡
ከክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር በተጨማሪም ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ ባለስልጣናት በፌደራል የጸጥታ አካላት ተይዘው እንደተወሰዱም ምንጮች ገልጸዋል፡፡ ይህ እርምጃም በክልሉ በተለይም ደግሞ በዋና ከተማው ጋምቤላ ተጨማሪ ውጥረት ማስፈኑ ነው የተገለጸው፡፡ በተመሳሳይ በጋምቤላ ከተማ የማረጋጋት ስራ ሲሰሩ የነበሩ የፌደራል የጸጥታ አካላት ከአኝዋክ ወጣቶች ጋር በተፈጠረ አለመግባባት በጸጥታ አካላት ላይ ጉዳት መድረሱም ዝግጅት ክፍላችን መዘገቡ የሚታወስ ነው፡፡
በክልሉ እየተባባሰ የመጣው የጸጥታ ችግር በቂ ትኩረት እየተሰጠው አይደለም የሚሉት ተንታኞች በተለይም ደግሞ ከጎረቤት አገር የመጡ የታጠቁ ኃይላት መኖራቸው ችግሩን የባሰ ውስብስብ እንደሚያደርገው ነው የሚገልጹት፡፡












