Home / ዜና / የግል ሚዲያዎች የምክክሩን ጉባኤ እንዳይዘግቡ እየተከለከሉ ነው

የግል ሚዲያዎች የምክክሩን ጉባኤ እንዳይዘግቡ እየተከለከሉ ነው

ከሦስት ቀናት በፊት የተጀመረውን የሀገራ ምክክር ጉባኤ፣ የግል ሚዲያዎች እና የዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ጋዜጠኛ በነጻነት እንዳይዘግቡ ገደብ እየተጣለባቸው መሆኑን ለሆርን ፍሪኩዌንሲ ተናግረዋል።

የምክክር ጉባኤውን መክፈቻ ጨምሮ ከመንግሥት ሚዲያዎች ውጭ ባለፉት ሦስት ቀናት የግል ሚዲያ እንዳይገቡ ተከልክለዋል። በዚህም የግል ሚዲያዎች ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በተገኙበት የተደረገውን የመክፈቻ ስነ ስርዓት ከኢቲቪ ወስደው እንደ ቀጥታ ስርጭት እንዲያስተላልፉ መደረጋችን ምንጮች ገልጸዋል።

በእለቱ በግል ሚዲዎች ጭምር በቀጥታ ስርጭት እየተላለፈ እንደሆነ ተደርጎ የቀረበው የመክፈቻ ስነ ስርዓት፣ ከኢቲቪ ቋት ተወስዶ ከትክክለኛው ሰዓቱ ሰዓታትን ዘግይቶ ነበር የተላለፈው።

ምንም እንኳን የግል ጣቢያዎች በቀጥታ ያስተላለፉት የመሰለው ዝግጅት ከኢቲቪ የተወሰደ ቢሆንም ኢቲቪ ራሱ እንደ ቀጥታ ስርጭት ያስተላለፈው ፕሮግራም፤ አንድ ሰዓት የዘገየ እንደነበር ምንጮች አረጋግጠዋል።

ከጉባኤው መክፈቻ ማግስትም የግል እና የውጭ ሚዲያ ጋዜጠኞች እንዳይዘግቡ ተከልክለዋል። በሦስተኛው ቀን ደግሞ የተወሰኑ ሚዲያዎች ተፈቅዶላቸው ሲገቡ፣ ሪፖርተር ጋዜጣን ጨምሮ የተመረጡ ሚዲያዎች እንዳይገቡ ገደብ ተጥሎባቸዋል።

ኮሚሽኑ ሁሉም ሚዲያዎች የምክክር ጉባኤውን ሂደት እንዲዘግቡ፣ ከ150 በላይ ጋዜጠኞችን አልሰልጥኖ ነበር። በልዩ ሁኔታ ጉባኤውን ለመዘገብ ተመርጠው የሰለጠኑ ጋዜጠኞች መካከል የተወሰኑት፣ የመግቢያ ባጅ ተሰጥቷቸዋል።

አብዛኞቹ ጋዜጠኞች ከሰለጠኑ በኋላ ባጅም ማግኘት ሳይችሉ ቀርተዋል ተብሏል። ባጅ የወሰዱትም ወደ ጉባኤው ቦታ እንዳይገቡ በደህንነት ሰዎች መከልከላቸውን ተናግረዋል።

አንድ የውጭ ሚዲያ ዘገቢ በስልጠናው ተሳትፎ ባጅ የወሰደ ቢሆንም፣ እንዳይገባ በር ላይ ባሉ የደህንነት አካላት መከልከሉን ገልጿል። በዚህም የጉባኤው ሂደት በአካል ተገኝቶ መመልከትና ዘገባ መሥራት አለመቻሉን ተናግሯል።

የግል እና የውጭ ሚዲያዎች የምክክር ጉባኤውን በነጻነት እንዳይዘግቡ ገደብ የተጣለባቸው፣ በቁጥጥር ሥራው የጠቅላይ ሚነስትር ጽ/ቤት ጣልቃ በመግባቱ መሆኑን ምንጮች ጠቁመዋል።

የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት በጉባኤው ሂደት ላይ ዋና የቁጥጥር አካል ሆኖ መምጣቱን የኮሚሽኑ ምንጮች ነግረውናል። በዚህም የራሱ የኮሚሽኑ ሰራተኞች ጭምር ምክክሩ ወደ ሚደረግበት አዲስ ኮንቬንሽን ሴንተር እንዳይገቡ እስከመከልከል የደረሰ ችግር ገጥሟቸዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *