አዲስ አበባ፡ በደቡብ አፍሪቃ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በመጤ ጠል እንቅስቃሴ አራማጆች የተቀመጠው የፈረንጆች ጁን 30 ቀነ ገደብ መጠናቀቁን ተከትሎ የጎዳና ላይ ሰልፍ ቢደረግም የተፈራው አልደረሰብንም ሲሉ ለዝግጅት ክፍላችን ተናገሩ።
ጁሃንስበርግን ጨምሮ ፕሪቶሪያ እና ደርባን የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ከሆርን ፍሪኩዌንሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ አንዳንድ ስፍራዎች ላይ አልፎ አልፎ ጥቃቶች እና ህገ ወጥ ድርጊቶች ቢኖሩም እንደተፈራው ጥቃት አልደረሰብንም፤ የጎዳና ላይ ሰልፉም ከሞላ ጎደል በሰላማዊ መንገድ ነው የተከናወነው ሲሉ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያዊያን ይህ ቀን ከመድረሱ አስቀድመው ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ በተገኘው አጋጣሚ ሲነገራቸው እንደነበር እና የሚዲያ ተቋማትም ያደረጉት ሰፊ ሽፋን ችግሮች ከመከሰታቸው አስቀድመው ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደነበረው አስታወቀዋል። ከዚሁ ጋር በተያያዘም ደግሞ ይህን ችግር በመፍራት ከወር በላይ ሱቃቸውን ዘግተው ከስራ ውጪ የሆኑ ኢትዮጵያዊያን መኖራቸውን እና ለተለያዩ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች እንደተዳረጉ አክለው ተናግረዋል።
በመላው ደቡብ አፍሪቃ ህጋዊ ባልሆነ መንገድ ወደ አገራችን ገብተዋል ባሏቸው የሌሎች አፍሪቃ አገራት ዜጎች ላይ አገሪቱን ለቀው እንዲወጡ የተቀመጠው ቀነ ገደብ በትናንትናው ዕለት ማለቁን ተከትሎ በርካታ ደቡብ አፍሪቃዊያን ወደ ጎዳና በመውጣት ሃሳባቸውን አስተጋብተዋል። በዕለቱም ሱቆች ተዘግተዋል፣ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴም በሰፊው ተስተጓጉሎ እንደነነበር ያነጋገርናቸው ኢትዮጵያዊያን ተናግረዋል። ከቀነ ገደቡ መጠናቀቅ አስቀድሞ የአንዳንድ አገራት መንግስታት ዜጎቻቸውን ከደቡብ አፍሪቃ ለማስወጣት ሙከራ አድርገዋል በዚህም ጋና ቀዳሚዋ ስትሆን ኡጋንዳ እና ማላዊም ይጠቀሳሉ።
በፕሪቶሪያ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኢምባሲም ጉዳዩን በሚመለከት ከቀናት በፊት የማስጠንቀቂያ መልዕክት ማስተላለፉ ይታወሳል። ይሁን እንጂ በደቡብ አፍሪቃ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ኢምባሲው ከሚገባው በታች እየሰራ እንደሆነ እና የውጭ ጉዳይ ሚንስትር እንዲሁም ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድም ጉዳዩን እንዲረዱልን እንጠይቃለን ሲሉም ተናገርዋል። በጉዳዩ ላይ በፕሪቶሪያ የኢትዮጵያ ኢምባሲ ማብራሪያ ከመስጠት ተቆጥቧል።
በትናንትናው ዕለት የተካሄደውን የጎዳና ላይ ሰልፍ በሰላማዊ መንገድ እንዲካሄድ የደቡብ አፍሪቃ መንግስት ከፍተኛ የጸጥታ ኃይል ያሰማራ ሲሆን፤ ከመንግስት የጸጥታ ተቋማት በተጨማሪም በግል ዘርፍ የተሰማሩ የጸጥታ አካላትም ተሳታፊ በመሆን ጉዳት እንዳይደርስ ጥበቃ ሲያደርጉ ተስተውሏል። ለዚህም ደግሞ በሚልዮን የሚገመት ራንድ ወጪ መደረጉ ተሰምቷል። የተለያዩ ሪፖርቶች እንደሚያመለክቱት ከተሰማራው የጸጥታ ኃይል አልፎ ግን አንዳንድ ስፍራዎች ግልጽ ዘርፊያ እና በድንጋይ በመወርወር ንብረቶችን የማውደም ጥቃት መድረሱም ተረጋግጧል።










