Home / ዜና / በደቡብ አፍሪቃ የኢትዮጵያ ኢምባሲ ለዜጎች የጥንቃቄ መልዕክት አስተላለፈ

በደቡብ አፍሪቃ የኢትዮጵያ ኢምባሲ ለዜጎች የጥንቃቄ መልዕክት አስተላለፈ

በደቡብ አፍሪቃ ፕሪቶሪያ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኢምባሲ በደቡብ አፍሪቃ የተቀጣጠለውን የመጤ ጠል እንቅስቃሴን ምክንያት በማድረግ በመጪዎቹ ቀናት ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚችል አዝማሚያ መኖሩን በመጥቀስ በደቡብ አፍሪቃ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አስታውቋል።

ኢምባሲው እንዳስታወቀው በመጪዎቹ ቀናት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይቻላል የተባለው እና በውጭ አገራት ዜጎች ላይ ሊደርስ የታሰበውን ጥቃት ለመከላከል የደቡብ አፍሪቃ መንግስት በቀጣይ ቀናት ጥበቃዎችን ሊያጠናክር መሆኑን አስታውቆ፤ ነገር ግን ኢትዮጵያዊያን እንቅስቃሴያቸው የተመጠነ እና ጥንቃቄ የተሞላበት እንዲሆን በጥብቅ አስታውቋል። ከዚህም በተጨማሪ ኢምባሲው ከደቡብ አፍሪቃ መንግስት ጋር በቅርበት በመወያየት ላይ እንደሚገኝም ይፋ አድርጓል። ሁሉም ኢትዮጵያዊ በአቅራቢያው በሚገኙ የመንግስት አካላት እና የኮሚኒቲ አደረጃጅቶች ጋር በቅርበት ግንኙነት እንዲያደርጉ እና መረጃ እንዲለዋወጡም መክሯል።

በደቡብ አፍሪቃ መጤዎችን በተለይም ደግሞ በህገ ወጥ መንገድ ወደ አገር ውስጥ ገብተዋል የተባሉ የሌሎች አገራት ዜጎችን የማስወጣት እና ከፍ ሲልም ጥቃት የመሰንዘር ተግባራት መጀመራቸው ዋል አደር ያለ ጉዳይ መሆኑ የታወሳል። በቅርቡ ደግሞ በእንቅሰቃሴው መሪዎች የተቀመጠው የፈረንጆች ሰኔ 30 ቀነ ገደብ እየተቃረበ መምጣቱን ተከትሎ ከፍተኛ ስጋት በውጭ አገራት ዜጎች ዘንድ እየተስተዋለ ይገኛል። ይህንንም ተከትሎ የደቡብ አፍሪቃ መንግስት የጥበቃ ኃይሉን እንደሚያጠናክር እና ዜጎችም በተባለው ቀን ምንም አይነት ጥቃት የመሰንዘር አዝማሚያ እንዳያሳዩ ጥብቅ ተዕዛዝ ቢያስተላልፍም ተቀባይነት ያገኘ አይመስልም። በጉዳዩ ላይ ከዝግጅት ክፍላችን ጋር ቆይታ ያደረጉ በደቡብ አፍሪቃ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እንደተናገሩት መጪው ጊዜ አስፈሪ መሆኑን እና የመንግስት የጸጥታ አካላትም የችግሩ ተሳታፊ መሆናቸው ችግሩን እንዳባባሰው ይናገራሉ።  

Sign Up For Daily Newsletter

Stay updated with our weekly newsletter. Subscribe now to never miss an update!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *