በብሔር ተኮር ግጭት ውጥረት ላይ በሚገኘው የጋምቤላ ክልል ውስጥ የሚኖሩ “ሐበሻ” ወይም “ደገኛ” ተብለው የተለዩዜጎች ለጥቃት እና ዛቻ መጋለጣቸውን ለሆርን ፍሪኩዌንሲ አስታውቀዋል።
በክልሉ በቅርቡ በአኝዋክ እና ኑዌር ብሔረሰቦች መካከል የተፈጠረው ግጭት፣ ከሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች ለስራ የሄዱወገኖች ላይ ስጋት እየደቀነ መጥቷል። አሁንም የቀጠለው ውጥረት በተለምዶ “ሐበሻ” ተብለው የሚጠሩ ወገኖች ላይግድያ፣ ዛቻና ወከባ እየተፈጸመ ነው ተብሏል።
ባለፉት ሁለት ሳምታት ውስጥ ብቻ ሦስት ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን ምንጮች ገልጸዋል።
ባለፈው ሳምንት ከዋና ከተማው ጋምቤላ ተነሰቶ ወደ ተርፋም በመጓዝ ላይ የነበረ ተሽከርካሪ መንገድ ላይ ጥቃት ደርሶበትአንዲት ወጣት ለህልፈት እንድትዳረግ ሆኗል። በጥቃቱ ሦስት ሰዎች መቁሰላቸው የተገለጸ ቢሆንም ቁጥሩ ከዚህም ሊልቅ እነደሚችል ተጠቁሟል። ከጥቃቱ በኋላ ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ አስቸጋሪ መሆኑን ምንጮች ለዝግጅት ክፍላችን አስታውቀዋል።
ከሁለት ሳምንት በፊት ደግሞ አንድ ወጣት በጋምቤላ ከተማ በስለት ጉዳት ደርሶበት ለህልፈት መዳረጉ የታወቀ ሲሆን፤ወጣቱ የተገደለው በክልሉ በተፈጠረው ውጥረት አንዱን ወገን ትደግፋለህ በሚል ሰበብ መሆኑን ምንጮች ተናግረዋል።
ከቀናት በፊት ሰኔ 27/2018 ዓ.ም በጋምቤላ ከተማ አንድ አሽከርካሪ መገደሉን ምንጮች ገልጸዋል። ግለሰቡ የተገደለውሲያሽከረክረው የነበረው ሲኖ ትራክ የተሰኘው ከባድ ተሽከርካሪ በቴክኒክ ብልሽት ምክንያት ከሌላ ተሽከርካሪ ጋር በመጋጨቱ እና በህይወት ላይ አደጋ በማድረሱ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ወገኖች ናቸው የተባሉ ሰዎች በክልሉ ምክር ቤት ፊት ለፊት፣ሹፌሩን ገድለው መኪናውን አቃጥለውታል። በዚህም በከተማዋ የሚኖሩ ከሌሎች አካባቢዎች ለስራ የሄዱ ሰዎችየመጠቃት ስጋት አይሏል።
ግድያዎቹ የተፈጸሙት በክልሉ መዲና ጋምቤላ ከተማ ውስጥ በቀን ጭምር መሆኑ ስጋቱን ከፍ አድርጎታል። ጉዳዩ ትኩረትተሰጥቶት መፍትሔ ካልተሰጠው ውጥረቱ ተባብሶ ይቀጥላል የሚል ስጋት ገብቷቸዋል።
በተፈጠረው ውጥረት “ሐበሻ” ተብሎ የሚለዩ ወገኖች ክልሉን ለቀው እንዲወጡ ጭምር የማስፈራሪያት አዝማሚያዎችእየታዩ ነው ተብሏል።
በክልሉ የተፈጠረውን ውጥረት ለመቆጣጠር ቀደም ብሎ፣ የሀገር መከላከያ ሠራዊት እና ፌደራል ፖሊስ በስፋትተሰማርተዋል። ይሁን እንጂ የክልሉ ብሔር ተኮር ግጭት አንዳንድ የአካባቢው ባለሥልጣናትና የጸጥታ ኃይሎችየተቧደኑበት ውስብስብ ጉዳይ በመሆኑ፣ እርምጃ ለመውሰድ አስቸጋሪ መሆኑን ምንጮች ጠቁመዋል።












