Home / ዜና / በደቡብ አፍሪቃ የኢኮኖሚ ተግዳሮት ከህገ ወጥ ፍልሰተኞች ጋር እንደማይገናኝ ፕሪዝዳንቱ አስታወቁ

በደቡብ አፍሪቃ የኢኮኖሚ ተግዳሮት ከህገ ወጥ ፍልሰተኞች ጋር እንደማይገናኝ ፕሪዝዳንቱ አስታወቁ

የደቡብ አፍሪቃው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ በቀጥታ ቴሌቪዝን ለህዝባቸው ንግግር ባደረጉበት ወቅት በአገሪቱ የሚታየው የኢኮኖሚ ተግዳሮት እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ከህገ ወጥ ፍልሰተኞች ጋር የሚገናኝ እንዳልሆነ አስታወቁ።

ፕሪዝዳንቱ በመግለጫቸው በአገር ውስጥ የሚገኙ የውጭ አገራት ዜጎች ህጋዊ ቢሆኑም ወይም በህገ ወጥ መንገድ ቢገኙም የሚጠየቁት በህግ አካላት እንጂ በማንኛውም ዜጋ ሊሆን እንደማይችል አስታውቀዋል። አያይዘውም በኢምግሬሽን ህግጋት ዘንድ ያለውን ክፍተት፣ ሙስና እና ብልሹ አሰራሮችንም አንስተው፤ መንግስታቸው እነዚህን ችግሮች በይፋ እንደሚያምን እና እንደሚቀበል ነገር ግን ችግሮችን ለማረም እየተሰራበት እንደሆነም አስታውቀዋል።

ዜጎች ድንበሮቻችን በትክክልም ጥብቅ ቁጥጥር እንደሚካሄድባቸው ይጠይቃሉ ያሉት ራማፎሳ፤ ማንኛውም የውጭ አገር ዜጋ በህጋዊ መንገድ ወደ ደቡብ አፍሪቃ መግባት እንዳለበት እና በህጋዊ መንገድም መቆየት እና መኖር እንደሚገባም አስታውቀዋል። ህገ ወጥ ፍልሰት የዓለም አገራት ችግር እንደሆነ በመግለጫቸው ያነሱት ፕሪዝዳንቱ ደቡብ አፍሪቃም የዚሁ ችግር ገፈት ቀማሽ ናት ብለዋል። አያየዘውም አገራቸው በመርህ ላይ የተመሰረተ ከለላ ለሚሹ የውጭ አገራት ዜጎች ግን አሁንም በራቸው ክፍት መሆኑን ጠቁመዋል።

“ደቡብ አፍሪቃዊያን መጤ ጠል አይደለንም” ያሉት ፕሬዚደንት ተገቢ እና ህጋዊ ሽፋን ያላቸው የሚመስሉ ጥያቄዎችን ያነገቡ እንቅስቃሴዎችን ባለመቀላቀል እና የአገሪቱን ሰላም ባለማደፍረስ ህዝባቸው እንዲታቀብ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ዜጎች የሚያነሷቸው እና ተገፍተናል የሚሉባቸውን ነጥቦች በተለይም ደግሞ በስራ፣ የህዝብ አገልግሎት ጫና፣ በንግድ እና በሌሎች የተለያዩ ዘርፎች ላይ የሚታየውን ችግር ለመፍታት መንግስታቸው ቁርጠኛ መሆኑን ራማፎሳ ተናግረዋል።

በደቡብ አፍሪቃ በመጪው የፈረንጆች ሰኔ 30 ቀን የተቆረጠለት እና ህጋዊ አይደሉም የሚባሉ የውጭ አገራት ዜጎችን የማስወጣት እንቅስቃሴ መኖሩ የሚታወስ ሲሆን፤ በዚህ ወቅትም ይህ መግለጫ መውጣቱ በተወሰነ መልኩ ለውጭ አገራት ዜጎች እፎይታ መሆኑን በደቡብ አፍሪቃ የሚኖሩ ከዝግጅት ክፍላችን ጋር ቆይታ ያደረጉ ሰዎች ተናግረዋል።

Sign Up For Daily Newsletter

Stay updated with our weekly newsletter. Subscribe now to never miss an update!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *