Home / ፖለቲካ / በራያ ሀገረ ስብከት ጥምቀት በአደባባይ አይከበርም ተባለ

በራያ ሀገረ ስብከት ጥምቀት በአደባባይ አይከበርም ተባለ

የሕወሓት ኃይሎች ራሳቸውን “መንበረ ሰላማ” ብለው በሰየሙ የኃይማኖት አባቶች በጋራ በፈጠሩት ሁከት በራያ ሀገረ ስብከት በተለይም በአላማጣ ከተማ የጥምቀት በዓል በአደባባይ እንደማይከበር ሆርን ፍሪኩዌንሲ ሰምቷል።

የጥምቀት በዓል ከመከበሩ በዋዜማው የሚከናወነው የከተራ በዓል በዛሬው ዕለት አለማክበሩን የሀገረስብከቱ እና የአካባቢው አመራሮች ለሆርን ፍሪኩዌንሲ አስታውቀዋል። ሀገረ ስብከቱ የዘንድሮው የጥምቀት በዓል ለማክበር አስቻይ ሁኔታዎች እንዲፈጠሩለት ቀደም ብሎ፣ በራያ አካባቢዎች ለተሰማራው የመከላከያ ሠራዊት ኮማንድ ፖስት ጥያቄ ቢያቀርብም እንዳልተሳካ ገልጿል።

የ’መንበረ ሰላማ’ አባላት ናቸው የተባሉት አካላት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ያቋቋመው፣ የራያ ሀገረ ስብከት አገልግሎት እንዳይሰጥ ካህናትን በማፈን፣ በመደብደብና በማስፈራራት ጫና እየፈጠሩ ነው ተብሏል። ከሰሞኑ ከህወሓት ታጣቂዎች በ ‘መንበረ ሰላማ’ ካልሆነ፣ በራያ ሀገረ ስብከት ጥምቀት እንዳይከበ አስቀድመው፣ በአገልጋዮችና ምዕመኑ ላይ ጫና ሲፈጥሩ ነበር ተብሏል።

የህወሓት ታጣቂዎች በአላማጣ ከተማና አካባቢው የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት በጋራ የሚያርፉበትን ባህረ ጥምቀት ቦታ ወታደራዊ ካምፕ አድርገውታል ተብሏል። ሀገረ ስብከቱ ጥምቀትን ለማክበር በህወሓት ታጣቂዎች የታፈኑ ካህናትን እንዲፈቱ እና ካምፕ የሆነውን ባህረ ጥምቀቱን ስፍራ በሚመለከት ወደ ነባር ይዞታው እንዲመለስ ለኮማንድ ፖስቱ ጥያቄ አቅርቦ እንደነበር ዝግጅት ክፍላችን የተመለከተው ደብዳቤ ያመላክታል።

ሀገረ ስብከቱ የህወሓት ተጣቂዎች የባህረ ጥምቀት ቦታውን ለቀው ካልወጡ፣ በዓሉን ማክበር አስቸጋሪ እንደሚሆን ለኮማንድ ፖስት በጻፈው ደብዳቤ አስቀድሞ አስጠንቅቆ ነበር። የ’መንበረ ሰላማ’ ቡድን ከአንድ ዓመት በፊት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ስር ራሱን የቻለ ሀገረ ስብከት የተቋቋመለትን የራያ አካባቢ ቤተክርስቲያናትን ለመጠቅለል በኃይል የተደገፈ እርምጃ መውሰዱን መቀጠሉ ተጠቁሟል።

የራያ ሀገረ ስብከት ራሱን ‘መንበረ ሰላማ’ ብሎ የሚጠራው ሲኖዶስ የተነጠሉ የትግራይ አካባቢ አባቶች ስብስብ ከህወሓት ታጣቂዎች ጋር በመቀናጀት፣ በካህናትና በምዕመናን ላይ በተቀናጀ ግፍ እና በደል በመፈጸም ላይ ይገኛል ሲል ባለፈው ዓርብ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

የህወሓት ታጣቂዎች ‘መንበረ ሰላማ’ መሪነት የሀገረ ስብከቱን ጽሕፈት ቤትን እና የወረዳ ቤተ ክህነቱን ቢሮዎች በኃይል በመቆጣጠር የቤተክርስቲያኒቱን ንብረቶችና ቅርሶች ዘርፈው ወታደራዊ ካምፕ አድርገዋቸዋል በማለት ከሷል። ይኸው የኃይማኖት አባቶች ቡድን የራያ ሀገረ ስብከት የተቋቋመው አካባቢውን ወደ አማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ለማካለል ነው የሚል ፕሮፓጋንዳ በመንዛት ሕዝቡን ለማደናገር እና ዓላማውን ለማሳካት ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል በማለትም አገረ ስብከቱ ኮንኗል።

በዚሁ ቡድን እና በህወሓት ታጣቂዎች ምክንያት ያለፈው የመስቀል ክብረ በዓል ሳይከበር ማለፉ ይታወሳል። ሀገረ ስብከቱ በአካባቢው ለተሰማራው ኮማንድ ፖስት በጻፈው ደብዳቤ፣ የደመራ ስፍራው በህወሓት ታጣቂዎች በመያዙ የመስቀል በዓል አለማክበሩን አስታውሷል።

ጉዳዩን በሚመለከት ከሕወሓት ወገን ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም። ምላሽ ባገኘን ጊዜ መረጃውን የምናጋራ ይሆናል።

Sign Up For Daily Newsletter

Stay updated with our weekly newsletter. Subscribe now to never miss an update!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *