Home / ፖለቲካ / በዋግ ኽምራ በደረሰ የድሮን ጥቃት በትንሹ የ40 ሚሊሻ አባላት ህይወት ማለፉ ተነገረ

በዋግ ኽምራ በደረሰ የድሮን ጥቃት በትንሹ የ40 ሚሊሻ አባላት ህይወት ማለፉ ተነገረ

መንግስት በስህተት መሆኑን ገልጾ ይቅርታ ጠይቋል

በአማራ ክልል በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር፣ ሰሃላ ሰየምት ወረዳ በባርዋ ቀበሌ ልዩ ስሙ “ፈፋ ድልድይ” ተብሎ በሚጠራው ንዑስ ከተማ አቅራቢያ በሚገኝ የሚሊሻ ካምፕ ላይ ትላንት ጥር 07 ቀን 2018 ዓ.ም በደረሰ የድሮን ጥቃት በርካታ ታጣቂዎችና ንፁሃን ዜጎች ለህልፈትና ለከፍተኛ የአካል ጉዳት መዳረጋቸው ተሰማ።

ጥቃቱ የተፈጸመው ትላንት ረፋድ 3፡30 ገደማ ሲሆን፣ በወቅቱ የመንግስት የሚሊሻ አባላት በካምፑ ውስጥ ምግብ በመመገብ ላይ እንደነበሩ ተገልጿል።

ሆርን ፍሪኩዌንሲ ከዞኑ የስራ ኃላፊዎች ባገኘችው መረጃ መሰረት፣ የሟቾች ቁጥር በአሁኑ ወቅት ከ40 በላይ መድረሱ ታውቋል። ከሟቾቹ በተጨማሪ በርካታ ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሰዎች ከፍተኛ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል። ጥቃቱ በመንግስት ድሮን አማካኝነት የተፈጸመ ሲሆን፣ የደረሰውን ጉዳት ተከትሎ የመንግስት የጸጥታ አመራሮች በአካባቢው ተገኝተው ማብራሪያ ሰጥተዋል።

አመራሮቹ በጥቃቱ ለደረሰው የሰው ህይወት መጥፋትና የአካል ጉዳት ማዘናቸውን ገልጸው፤ “ጥቃቱ ለጠላት (ለፋኖ ታጣቂዎች) ታቅዶ የነበረ ቢሆንም በስህተት በሚሊሻ አባላት ላይ ያረፈ ነው” በማለት ይቅርታ መጠየቃቸውን የደረሰን መረጃ ያመለክታል። ለፋኖ ታጣቂዎች ታስቦ የተወነጨፈው ጥቃት የራሱን የመንግስት የሚሊሻ አባላትንና በአቅራቢያው የነበሩ ንጹሃንን ሰለባ ማድረጉ ክስተቱን እጅግ አሳዛኝ አድርጎታል ነው ያሉት።

በአካባቢው የሚገኙ ነዋሪዎችና የተጎጂ ቤተሰቦች በደረሰው ድንገተኛ አደጋ ከፍተኛ ድንጋጤና ሃዘን ውስጥ እንደሚገኙ ተገልጿል መንግስት ስለደረሰው ጉዳት ዝርዝር መረጃ እስካሁን በይፋዊ ገጾቹ ላይ ያወጣው መግለጫ ባይኖርም፣ በአካባቢው የሚገኙ የዞንና የወረዳ አመራሮች ግን ከህዝቡ ጋር ውይይት በማድረግ ላይ መሆናቸው ታውቋል። የሞቱ የሚሊሻ አባላት በዛሬው እለት ወደየመጡበት አካባቢ እየተላኩ የቀብር ስነስርዓታቸው እየተፈጸመ መሆኑ ተመላክቷል። በትላንትናው እለት በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር አበርገሌ ወረዳ 03 ቀበሌ በልታርፍ ጎጥ ውስጥ በሚገኝ አንድ መኖሪያ ቤት ውስጥ በተከሰተ የመድፍ ቁምቡላ ፍንዳታ የ5 ሰዎች ሕይወት ስለማለፉ መዘገባችን ይታወሳል።

Sign Up For Daily Newsletter

Stay updated with our weekly newsletter. Subscribe now to never miss an update!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *