ከዚህ ቀደም የቀረቡ ጥያቄዎች በአግባቡ ካልተመለሱ ሁለተኛ ዙር የሥራ ማቆሞ አድማ እንደሚቀጥል የኢትዮጵያ ጤና ባለሙያዎች ንቅናቄ ለመንግሥት በጻፈው ደብዳቤ አሳስቧል።
መንግሥት በተለይ አንገብጋቢ ለተባሉ ለጤና ባለሙያዎች ጥያቄዎች በአፋጣኝ ምላሽ ካልሰጠ፣ ሁለተኛው ዙር የሥራ ማቆም አድማ ታህሳስ 1/2018 ዓ.ም ይጀምራል ተብሏል።
ንቅናቄው ከዚህ ቀደም በግልጽ ተዘርዝረው የቀረቡ ጥያቄዎች አለመመለሳቸውን በመግለጽ እና አሁንም በግልጽ ባስቀመጣቸው የ12 ነጥቦች ምላሽ ከጤና ሚንስትርም ሆነ ከሚመለከታቸው አካላት የማይሰጥ ከሆነ ለቀጣይ ዙር የስራ ማቆም አድማ እና ሌሎች እርምጃዎችንም እንደሚወስዱ አስታውቋል፡፡
በአስቸኳይ መመለስ አለባቸው የተባሉ ጥያቄዎች መሆናቸው ለንቅናቄው ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለሆርን ፍሪኩዌንሲ ገልጸዋል። በአስቸኳይ መመለስ አለባቸው የተባለለ ጥያቄዎች፣ ከደመወዝና ጥቅማ ጥቅም ጋር የተያያዙ መሆናቸው ተመላክቷል።
አንደኛው አንገብጋቢ ነው የተባለው ጥያቄ በአዲሱ የደሞዝ ስኬል በሁሉም የጤና ተቋማት እና ክልሎች በአስቸኳይ እንዲተገበር እና ለጤና ባለሞያዎች በተለየ ሁኔታ በድጋሚ የደሞዝ ማሻሻያ ይደረግ የሚል ነው፡፡
ሁለተኛው ደግሞ የትርፍ ሰዓት ክፍያ በአዲሱ የደሞዝ ስኬል እና መመሪያ መሰረት ከመስከረም ጀምሮ ታሳቢ ተደርጎ እንዲከፈል የሚጠይቅ ነው፡፡ የጤና ባለሙያዎች የትርፍ ስዓት ክፍያ በአስቸኳይ በሀገር አቀፍ ደረጃ እንዲጀመር እና በነባሩ ደሞዝ የተከፈላቸውም ቀሪው ታስቦ እንዲከፈላቸው ንቅናቄው አሳስቧል፡፡
ሦስተኛው አንገብጋቢ ጥያቄ 30 ዓመት ሳይቀየር የቆየው የቤት፣ የተጋላጭነት፣ የሙያ እና የመሳሰሉት የጤና ባለሞያዎች የጥቅማ ጥቅም ማሻሻያ በአስቸኳይ ይደረግ የሚል ነው፡፡ የጤና ባለሞያዎችን ተሳቢ ያደረገ ስርዓት ከመዘርጋት ረገድ በመንግሥት በኩል ያሉ፣ ቸልተኝነቶች እንዲታረሙ ንቅናቄው ጠይቋል፡፡
መንግሥት የገባው ቃል አልፈጸመም በሚል ለሁለተኛ ዙር የሥራ ማቆም አድማ፣ ጥያቄዎቹን ለመመለስ የ20 ቀን ጊዜ ገደብ ተሰጥቶታል። አንገብጋቢ ተብለው የተለዩት ጥያቄዎች በሚቀጥሉት 20 ቀናት ካልተመለሱ፣ ባለሙያው በመንግሥት ላይ ጫና የሥራ ማቆም አድማና ሌሎች ሕጋዊ እርምጃዎችን ይወስዳል ተብሏል።
ለመንግሥት በተደጋጋሚ እየቀረበ የሚገኘው ጥያቄ፣ ኢኮኖሚያዊና ሙያዊ ብቻ መሆኑን የእንቅስቃሴው አስተባባሪ የኢትዮጵያ ጤና ባለሙያዎች ንቅናቄ አስታውቋል። የጤና ባለሙያዎች ጥያቄ በመንግሥት በኩል እንደሚባለው ፖለቲካዊ አንደምታ ያለው አለመሆኑን ንቅናቄው አስታውሷል።
የጤና ባለሙያዎች ከደመወዝ፣ ጥቅማ ጥቅም፣ የጤና ስርዓት ለውጥና ከሥራ ቦታ ደህነት ዋስትና ጋር የተያያዙ ጥያቄዎችን አንስተው ከሰባት ወራት በፊት የሥራ ማቆም አድማ መምታታቸው ይታወሳል።ጥያቄዎች የቀረቡበትን የጤና ባለሙያዎች የሥራ ማቆም አድማ ተከትሎ፣ መንግሥት የቀረቡትን ጥያቄዎች ደረጀ በደረጃ ለመፍታት ተስማምቶ ነበር።
ይሁን እንጂ አሁንም መሰረታዊ ጥያቄዎች አለመፈታታቸውን የንቅናቄው አመራሮች ተናግርዋል። መንግሥት በገባው ቃል መሰረት የቀረቡለትን ጥያቄዎች ከመፍታት ይልቅ፣ ከሕግ አግባብ ውጪ ያልተከፈሉ የባለሙያዎችን የትርፍ ጊዜ ክፍያ ማስከፈል አልቻለም ተብሏል።










