Home / ማህበራዊ / የማርበርግ ቫይረስ ስርጭት በአዲስ አበባ በብዛት እየታየ ነው

የማርበርግ ቫይረስ ስርጭት በአዲስ አበባ በብዛት እየታየ ነው

የማርበርግ ቫይረስ በሽታው ለመጀመሪያ ጊዜ በጅንካ ሆስፒታል መታየቱ ከተገለጸ በኋላ፣ በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ከተማ በብዛት እየተዛመተ መሆኑን የጤና ባለሙያዎች ለሆርን ፍሪኩዮንሲ ገልጸዋል።

በከተማዋ ይህ ቫይረስ የተገኘ ቢሆንም እስካሁን ህይወቱ ያለፈ ሰው እንደሌለ ገልጸው፤ ሕክምናው በልዩ ማቆያ ማዕከላት እየተሰጠ እንደሆነም ተመላክቷል።

የጤና ባለሙያዎቹ እንደሚያስረዱት፣ በአዲስ አበባ ያለው የስርጭት መጠን ከጅንካ እና አካባቢዋ በእጅጉ እንደሚልቅ የሚያስረዱት የጤና ባለሙያዎች፤ ይህ ሁኔታ ከፍተኛ ስጋት ውስጥ እንደከተታቸው እና ለበርካታ ሰዎች የላብራቶሪ ምርመራ እየተደረገ መሆኑንም አክለዋል።

ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የጤና ባለሙያዎች ለዝግጅት ክፍላችን እንደተናገሩት፤ የቫይረሱ በብዛት መዛመት ዋነኛ ምክንያት የአዲስ አበባን የትራንስፖርት ሁኔታ እንደሆነ ጠቁመዋል።

በከተማዋ አብዛኛው ነዋሪ ከቦታ ወደ ቦታ ለመንቀሳቀስ ርቀትን ባልጠበቀ እና በእጅጉ በተጠጋጋ ሁኔታ የሚጓጓዝ በመሆኑ፣ ይህ ቀጥተኛና ቅርብ ንክኪ ቫይረሱ ያለገደብ እንዲስፋፋ ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረ ተብራርቷል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ በሰጡት መግለጫ ተጨማሪ 2 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን አሳውቀዋል።

በዚህም መሰረት፣ ቫይረሱ እስካሁን በድምሩ 6 ሰዎች ላይ መገኘቱን ሚኒስትሯ ገልጸዋል። ይሁን እንጂ፣ እነዚህ ስድስቱ ታማሚዎች በምን አጋጣሚ እና ስፍራ በበሽታው እንደተያዙ ይፋ አላደረጉም። ከጤና ባለሙያዎች ባገኘነው መረጃ መሰረት በሕብረተሰቡ ዘንድ ጥንቃቄ ካልተደረገ በቀጣይ ከፍተኛ ስርጭት እንደሚኖር እና የጉዳቱም መጠን እንደሚጨምር ለማወቅ ተችሏል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *