በአማራ ክልል ክፍት የስራ ቦታ በሚል ሸዋጅ ማስታወቂያ ነው ቅጥሩ የሚካሄደው
የሀገር መከላከያ ሠራዊት ከሰሞኑ ያወጣው ወታደራዊ ሰልጣኝ ምልመላ ተከትሎ፣ በተለያዩ አካባቢዎች ወጣቶች በግዳጅና በጫና ተይዘው እየገቡ መሆኑን ሆርን ፍርኩዌንሲ ሰምቷል።
አዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች ወጣቶች በግዳጅ ለወታደራዊ ስልጠና እየተመለመሉ መሆኑን ዝግጅት ክፍላችን ባደረገው ክትትል ተረድቷል። አንድ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ወንድማቸው ከመሃል መገናኛ፣ ከሌሎች ወጣቶች ጋር በጅምላ በወታደራዊ ፓትሮል ተጨኖ ለወታደራዊ ምልመላ ጊዜያዊ ካምፕ መግባቱን ለሆርን ፍርኩዌንሲ ገልጸዋል።
በግዳጅ ለወታደራዊ ምልመላ የታፈሰው ወንድማቸው፣ በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ አሸዋ ሜዳ አካባቢ በሚገኝ በአንድ መንግሥታዊ መጋዘን ውስጥ እንደሚገኝ ተናግረዋል። ከመገናኛ የታፈሰው ወንድማቸው በኦሮሚያ ክልል በኩል ተመልማይ ሆኖ፣ ለመከላከያ ሠራዊት ተላልፎ ሊሰጥ መሆኑን ለዝግጅት ክፍላችን መረጃውን ያደረሱን ግለሰብ ጠቁመዋል።
ወጣቶች በየአካባቢው በሚኒሻ እየታደኑ ለወታደራዊ ምልመላ የሚቀርቡት፣ መከላከያ ሠራዊት ለክልሎች የሰጠውን ኮታ ለመሙላት ነው ተብሏል።
የመከላከያ ሠራዊት ምልመላ በየአካባቢው የሚካሄደው ‘የሥራ ዕድል’ በሚል ማስታወቂያ ነው። ይሁን እንጂ በተለይ የእርስ በእርስ ጦርነት ባለባቸው አማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች፣ ወጣቶች እንደከዚህ ቀደሙ ለውትድርና ምልመላ እምብዛም ፍላጎት አያሳዩም። ይህንንም ተከትሎ በርካታ የኃይል እርምጃዎች እና በግድ አፈሳዎች ይከናወናሉ፡፡
ከሰሜኑ ጦርነት ብዙም ሳያርፍ ሌላ የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ በገባው አማራ ክልል፣ ወታደራዊ ምልመላው የሚካሄደው በሥራ ዕድል ማስታወቂያ ማማለያ ነው። በሥራ ዕድል ማስታወቂያ ሥም የቀረበው ወታደራዊ ምልመላ ለክልሉ የተሰጠው ኮታ ለመሙላት በሚፈለገው ልክ ባለመሄዱ፣ በየመንደሩ ጫና የተሞላበት ምልመላ እየተካሄደ መሆኑን ባደረግነው ክትትል ተረድተናል።
በኦሮሚያ ክልልም በተመሳሳይ የወታደራዊ ምልመላ ኮታውን ለመሙላት ከክልሉ አልፎ በአዲስ አበባ ከተማ ጭምር በግዳጅ ሥራ ፈላጊ ወጣቶች ይታፈሳሉ። በክልሉ ወታደራዊ ምልመላ በሚኖርበት ወቅት ከተሞችን ጨምሮ ተማሪዎችን ጨምሮ ወጣቶች በስፋት እንደሚታፈሱ ሲዘገብ ቆይቷል፡፡
ህጻናትን ጨምሮ ወጣቶች በግዳጅ ለውትድርና እንደሚመለመሉ የአሜሪካ መንግሥት ከሰሞኑ በሰዎች ዝውውር ጋር በተያያዘ ባወጣው ኢትዮጵያን በሚመለከት ሪፖርት ላይ ተገልጿል። የኢትዮጵያ መንግሥት ሕጻናትን በግዳጅ ይዞ ለውትድርና አገልግሎት የመመልመል ድርጊቶችን እንዲያቆም የአሜሪካ መንግሥት በሪፖርቱ አሳስቧል።
መንግሥት ባለስልጣናትን ጨምሮ በሰዎች ዝውውር እና ሕጻናትን ለውትድርና አገልግሎት በማሰማራት በሚሳተፉ አካላት ላይ ምርመራ በማድረግ ጥብቅ ርምጃ እንዲወስድ በሪፖርቱ ምክረ ቀርቦለታል።










