Home / ማህበራዊ / የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሐሰተኛ የትምህርት መረጃ ያላቸውን ሰራተኞች ምደባ ፈጽሟል ተባለ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሐሰተኛ የትምህርት መረጃ ያላቸውን ሰራተኞች ምደባ ፈጽሟል ተባለ

የአገሪቱ ከፍተኛ የስልጣን ባለቤት የሆነው የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ጽሕፈት ቤት በቅርቡ አዲስ ሪፎርም መስራቱን ተከትሎ በመስሪያ ቤቱ ውስጥ የሐሰተኛ የት/ት መረጃ ይዘው ሲያገለግሉ የነበሩትን ሰራተኞችን እንደገና የስራ ምደባ መስጠቱን የሆርን ፍሪኩዌንሲ ምንጮች አስታውቀዋል።

በአፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ እና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ተጠሪ የሆኑት ተስፋዬ ቤልጅጌ በበላይነት የሚመሩት ሪፎርም በርካታ ሰራተኞችን ከነበሩበት የስራ ኃላፊነት እንዲነሱ እንዲሁም ከስራም እንዲሰናበቱ ማድረጉን ለማወቅ ተችሏል። ከዚህም ጋር ተያይዞ ለበርካታ ዓመታት የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ በመሆን ሲያገለግሉ የነበሩት ምስራቅ መኮንን (ዶ/ር) ከኃላፊነታቸው መነሳታቸውም ምንጮች አረጋግጠዋል።

በአንጻሩ ደግሞ በተካሄደው ሪፎርም በጽ/ቤቱ ውስጥ የሐሰተኛ የትምህርት መረጃ ያላቸውን፣ ከስራቸው ጋር ተዛማጅነት የሌለው የመንፈሳዊ ት/ት ዲግሪ ያላቸውን ሰዎች በስውር የስራ ምደባ እንዲሰጣቸው መደረጉ ታውቋል። የሪፎርሙ ዓላማ እምብዛም ግልጽ አይደለም የሚሉት ምንጮች፤ ያሏቸው የትምህርት ማስረጃዎች አንድም ለመንግስት መስሪያቤት አይሆንም ሌላም ደግሞ ሐሰተኛ ናቸው በሚል በመጀመሪያ ዙር ወደ ሲቪል ሰርቪር ዝርዝራቸውን አዘዋውሮ ነበር። ይሁን እንጂ በአሁኑ ሰዓት ሰዎች ምደባ እያገኙ ሲሆን በህግ መጠየቅ ሲገባቸው እንዴት ምደባ ውስጥ ገቡ የሚል ጥያቄም ከሰራተኞች ዘንድ እየተስተጋባ ነው።

በጽ/ቤቱ ውስጥ አቶ ፒተርዘግሬት ለይኩን የተባሉ ግለሰብ የመንፈሳዊ ዲግሪ ብቻ ያላቸው መሆኑ በመታወቁ ከምደባ ውጪ ተደርገው የነበረ ቢሆኑም ግልጽ ባልሆነ ምክንያት በጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ ተወካይ አማካኝነት ምደባ እንደተሰጣቸው እና የመንግስት ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባለሙያ እንደተደረጉም ምንጮች ለዝግጅት ክፍላችን አረጋግጠዋል።

በተካሄደው ሪፎርም 450 የተቋሙ ሰራተኞች ምደባ እንደተካሄደ ለማወቅ ተችሏል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *