Home / ፖለቲካ / ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኤርትራ ጋር ጦርነት ከተቀሰቀሰ “ማንም አያቆመንም” አሉ

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኤርትራ ጋር ጦርነት ከተቀሰቀሰ “ማንም አያቆመንም” አሉ

ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውሏቸው በሰጡት ማብራሪያ ከቀይ ባህር እና ከወደብ ጋር ለተነሳላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ ጉዳዩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረው፤ ጦርነት ከተቀሰቀሰ ግን ማንም አያቆመንም ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

በቀይ ባህር ጉዳይ ለቀረቡላቸው ተደራራቢ ጥያቄዎች ጠቅላይ ሚንስትሩ በሰጡት ምላሽ ኤርትራን አስጠንቅቀዋል፡፡ ጠ/ሚሩ ለኤርትራ ባሰተላለፉት መልዕክት “ውጊያው ከተነሳ ውጤቱ ግልጽ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ እዬዬ አይሰራም” ብለዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ጦርነት “ከገባን ግን አስተማማኝ አቋም ነው ያለን ማንም አያቆመንም” ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ በቀይ ባህር ላይ በተለይም በአሰብ ላይ ያነሳችው ጥያቄ ምላሽ ማግኘቱ አይቀሬ መሆኑን በመጥቀስ፣ ኤርትራ ለድርድር ዝግጁ እንድትሆን አሳስበዋል፡፡ ኢትዮጵያ ከቀይ ባህር የተገለለችበት ሂደት ላይ የህጋዊ አግባብነት ጥያቄ ያነሱት አቢይ፣ ከዚህ በኋላ “ተገፍቶ” መቀጠል አይኖርም ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ የቀይ ባህር ጥያቄ የማይቀለበስ መሆኑን በመግለጽ፣ ለአሜሪካ፣ ቻይና፣ ራሺያ፣ አውሮፓና አፍሪካ እንዲያደራድሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ አቢይ በመልዕክታቸው “ቅድሚያ የምንሰጠው ለሰላምና ንግግር ስለሆነ እባካችሁ ሽምገሉና መፍትሔ አምጡልን” በማለት የጣልቃ ገብነት ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ያለአግባብ ያጣችውን ቀይ ባህር “30 ዓመት ያስፈልጋታል ብዬ አላስብም” ብለዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ቀይ ባህርን ያጣችበት ሂደት በካቢኔም፣ በፓርላማ ይሁን በሌላ ተቋማዊ ውሳኔ መሰረት እንደሌለው አስታውሰዋል፡፡

በወቅተቱ ኢትዮጵያ የባህር በር አልባ ያደረጋት ውሳኔ ሲወሳን ወሳኝ አካል ካልነበረ “ማን ወሰነው የሚለው የህልዉና ጉዳይ ነው” ብለዋለ፡፡ አሰብን በተመለከተ ወዳጅ በነበሩበት ወቅት ከኤርትራው ፕሬዝዳንት ጋር መነጋገራቸውን የጠቆሙት አቢይ፣ የኤርትራ ባለሥልጣናት ባልታወቀ ምክንያት በር መዝጋታቸውን ገልጸዋል፡፡

ከኤርትራ ጋር በተደረገ ንግግር የአሰብ አፋር ኢትዮጵያ መስመር መጠገኑን ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ “በግልጽ ባላወቅነው መንገድ ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ አልነበሩም” ብለዋል፡፡ በዚሁ ጉዳይ የኢትዮ-ኤርትራ ድንበር ብዙውም ሳይቆይ መዘጋቱን የገለጹ ሲሆን፣ የልዩነቱ መስፋት ዋና ምክንያት ግን የፕሪቶሪያው ሰላም ስምምነት ነው ብለዋል፡፡

“የቀይ ባህር ጉዳይ ህጋዊ፣ ታሪካዊ፣ መልከዓ ምድራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄ ነው ብለን እናምናለን” ሲሉም አክለዋል። አቢይ “ኢትዮጵያ ተዘግቶባት መኖር አትችልም” የሚል አቋም ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ለኤርትራ ባለሥልጣናት መግለጻቸውን አስታውሰዋል፡፡

ለዚህም “ከአምስት ዓመት በፊት ባህር ኃይል ያቋቋምነው እንዲዋኝ አይደለም” በማለት የባህር ኃይል የተቋቋመበትን ምክንያትም በጨረፍታ ጠቅሰዋል፡፡ ኢትዮጵያ የባህር ኃይል ያቋቋመችው በጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ እና በፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ላይ የተመሰረተው ግንኙነት ጥሩ በነበረበት ወቅት ነው፡፡

ከጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ንግግር አስቀድሞ የኤርትራው የማስታወቂያ ሚንስትር የማነ ገ/መስቀል ኢትዮጵያ አሰብ እና ምፅዋን ከኢትዮጵያ ጋር የሚያገናኝ የባቡር ሀዲድ ለመገንባት ዝግጅት ላይ መሆኗ መዘገቡን ተከትሎ ‹‹ብላ ያልተባለ ጨልፉልኝ ይላል›› በሚል የማጣጣል ንግግራቸውን በኤክስ ገጻቸው አስነብበዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *