Home / ቴክኖሎጂ / ቢሮክራሲያችን ሳይሻሻል “ዲጂታይዜሽን” በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ነው፡፡

ቢሮክራሲያችን ሳይሻሻል “ዲጂታይዜሽን” በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ነው፡፡

በቅርቡ በተለይም ካለፉት ሁለት ሶስት አመታት ወደዚህ ስለመንግስት አገልግሎቶች ‘ዲጂታይዜሽን’ ፣’ዲጂታል ኢትዮጵያ’ ፣ ‘ዲጂታል ሆኗል’ ፣ ‘ከወረቀት ነጻ አገልግሎት’ ወዘተ የሚሉ ቃላትን መስማት የተለመደ ሆኗል። ህዝቡም ሳይወድ በግድ “ዲጂታይዝድ” እንዲሆን እየተገደደ ነው። (ቋንቋውን በተመለከተ የቋንቋ ምሁራን ቢተቹት መልካም ነው)። እኔ ግን እንደ አንድ የመዲናዋ ነዋሪ ስለዲጂታይዜሽን ያለኝም ምልከታ ላካፍል ወደድኩ። በተለይም ዲጂታይዜሽን ምንድነው? ለምንስ ይጠቅማል? ምን ያህል እየተጠቀምንበት ነው? ቀድሞ ከነበሩ (የወረቀት አሰራሮች) በምን ተሻለ?

ዲጂታይዜሽን ምንድነው?

ዲጂታይዜሽን በወረቀት ይሰሩ የነበሩ ጽሁፎችን ፣ ፎቶዎችን ወይንም ሌሎች ዶክመንቶችን ወደ ኮምፒውተራዊ አሰራር መቀየር ተብሎ ሊተረጎም ይችላል። ይህም አሰራር ከኢንተርኔት መስፋፋት ጋር ተያይዞ በርካታ ነገሮች በርቀት ለማስጨረስ ይጠቅማል ተብሎ ይታሰባል።

የዲጂታይዜሽን ጥቅምስ ምንድነው?

የዲጂታይዜሽን ጥቅሞች በርካታ ሊሆኑ ቢችሉም ከመንግስታዊ አገልግሎቶች አንጻር የሚከተሉት መጥቀስ ይቻላል። አንደኛውና ዋነኛው ለመንግስታዊ አገልግሎት የሚሰጠው ጥቅም አገልግሎቶችን ማቀላጠፍ ነው። ይህንንም ሊያሳካ የሚችለው የድግግሞሽ ስራዎችን በመቀነስ፣ የቢሮክራሲ ማነቆዎችን ማሳነስ ፣ የወረቀት ዶክመንት መፈለግና ማገላበጥን በመቀነስ እንዲሁም ያሉትን መረጃዎች (ፋይሎች) በስርዓት ለማስቀመጥ በማገዝ አሰራሮቹ እንዲቀላጠፉ ያግዛል። ይህም ማለት አንድ አገልግሎት ሰጪ ሰራተኛ የሚሰጠውን አገልግሎት ያለ ብዙ መንገላታት ለተጠቃሚው መስጠት እንዲችል ያደርገዋል። ለምሳሌ አንድ የቀበሌ መታወቂያ ሊያሳድስ የሚፈልግ ዜጋ ቢኖር አገልግሎት ሰጪው የግለሰቡን ስም ወይንም ሌላ መለያ ብቻ በመጠቀም ፋይል ማገላበጥ ሳያስፈልገው በቀላሉ ከኮምፒውተሩ ላይ በመፈለግ መቀየር የሚገባቸውን (እንደጊዜ ፣ ፎቶ የመሳሰሉ) ነገሮችን ብቻ ቀይሮ መታወቂያውን አድሶ ሊሰጠው ይችላል። (መታወቂያ ማደስ ለምሳሌ የቀረበ ነው)፡፡ ይህም አሰራር ሊወስድ የሚችለው ጊዜ እጅግ በጣም አጭር ከመሆኑም በላይ ብዙ ፈራሚዎችን ስለማይጠብቅ ሂደቱ ፈጣን ይሆናል።

ሁለተኛው ጠቀሜታው ደግሞ ዜጎች አገልግሎቶችን በቀላሉ ማግኘት እንዲችሉ ማድረጉ ነው። ለምሳሌ ያክል አንድ አገልግሎት ፈላጊ ዜጋ የገቢ ግብር ለማሳደስ ቢፈልግ ወደ መንግስት መስሪያ ቤት መምጣት ሳያስፈልገው መረጃውን በርቀት (online) በማስገባት ፣ የተጓደሉ ነገሮች ካሉ በማስተካከል ፣ ከአገልግሎት ሰጪዎች ጋር በመነጋገር እንዲሁም ቀጠሮ በማስያዝ በርካታ አገልግሎቶችን ማግኘት ይችላል። ይህ መሆኑ ተገልጋይ ዜጋ ቢሮ ሄዶ ከመሰለፍ፣ ከትራንስፖርት ወጪ ፣ ከመመላለስ በእጅጉ የተሻለ አገልግሎት እንዲያገኝ ያደርገዋል። (ይህንን ስል አገልግሎት ፈላጊ ሆናችሁ መንግስት ቢሮ የሄዳችሁ ሰዎች እንደምትረዱኝ በመተማመን ነው። መንግስት መ/ቤት ‘ስራ የማይሰራበት ፣ አሰልቺ ፣ የሚያማርር’ የሚል ትርጓሜ እንደሚሰጠው ሁላችሁም ታውቃላችሁ።)

ከላይ ከተጠቀሱት በተጨማሪ የመንግስትንና የህዝብን ወጪ በመቀነስ፣ ግልጽነትን በማበረታታ፣ ሙስናን በመቀነስ ወዘተ የተገልጋዩንና የአገልጋዩን ህይወት ያቀላል፤ ስራን ያፋጥናል፤ ብሎም ህዝብ በመንግስት ላይ ያለውን አመኔታና ደስተኝነት ይጨምራል።

ምን ያህል እየተጠቀምንበት ነው?

ከላይ የተጠቀሱት የዲጂታይዜሽን ጥቅሞች ሲሆኑ አሁን ደግሞ በሀገር አቀፍ ደረጃ እንዴት እየተጠቀምንበት እንዳለ ዳሰሳየን አቀርባለሁ። በአሁኑ ጊዜ ሁሉም በሚባል ደረጃ ያሉ የመንግስት መስሪያ ቤቶች አገልግሎቶች ሁሉ “ዲጂታይዝድ” ናቸው፤ ወይም ነው ብለው ያስተዋውቃሉ። ከመታወቂያ ማሳደስ እስከ ቦሎ ማውጣት/ማሳደስ፣ ግብር መክፈልና ገቢን ማሳወቅ፣ ድርጅት መክፈትና መዝጋት … ሁሉም የሚባሉ አገልግሎቶች “ዲጂታይዝድ” ናቸው።

በሀገራችን ‘ዲጂታይዝድ” ሲባል ግን “ግማሽ ዲጂታይዝድ፤ ግማሽ የወረቀት ስራ” ማለቱ ሳይሻል አይቀርም። በምሳሌ ላብራራ፡፡ አንድ መስሪያ ቤት ሄዳችሁ አገልግሎት ስትጠይቁ አገልግሎታችን ዲጂታይዝድ ስለሆነ …. የሚባል ዌብሳይት ገብታችሁ ዶክመንቶችን ስካን አድርጋችሁ አስገብታችሁ፣ ቀጠሮ ተሰጥቷችሁ፣ በቀጠሮ ትመለሳላችሁ ትባላላችሁ። መረጃዎችን ካስገባችሁ በኋላ ቀጠሮ ብትጠብቁ ሳምንት ወይንም ከዚያ በላይ ስለሚያልፈው ጉዳያችሁ የት እንደደረሰ ለመጠየቅ መስሪያ ቤቱ ተመልሳችሁ ትሄዳላችሁ። የሲስተም ችግር ተፈጥሮ ነው ተብላችሁ ቀጠሮ ትይዛላችሁ። በቀጠሯችሁ መሰረት ዶክመንቶቻችሁን ይዛችሁ ስትመለሱ ታይቶ ተሟልቷል ወይንም አልተሟላም ተብላችሁ ወይ ወደ ቤታችሁ አልያም ወደ ፈራሚ አካላት ትወስዳላችሁ። ይህን ስታደርጉ “ፈራሚው የለም” ፣ “መዝገብ ቤት ተዘግቷል”፣ “የኮፒው ብዛት አንሷል”፣ “የመዝገብ ቤት ፋይላችሁ ጠፍቷል” ልትባሉ ትችላላችሁ፡፡ እድለኛ ሆናችሁ ይህ ሁሉ ቢሳካ የአገልግሎት ክፍያ የምትከፍሉት በባንክ ፣ በቴሌብር ወይንም በጥሬ ገንዘብ ነው ትባላላችሁ። በባንክ ወይንም በቴሌብር ከሆነ ገንዘቡ መግባት ያለበት ከራሳችሁ አካውንት ነው ትባላላችሁ። ይህን ሁሉ ስትጨርሱ ቀናትን ብሎም ሳምንታትን ይወስዳል። በግሌ ‘ዲጂታይዝድ’ የሆኑ በርካታ አገልግሎቶችን ተተቅሜያለሁ። የተጎዳሁት እንጂ የተጠቀምኩት የለም።

ቀድሞ ከነበሩ (የወረቀት አሰራሮች) በምን ተሻለ?

የዚህ ጽሁፍ ዋነኛ መነሻ ወደሆነው ነጥቤ ልመለስ። ዲጂታይዜሽን አገልግሎት ከቀድሞ (የወረቀት) አገልግሎት በምን ተሻለ? እኔ አልተሻለም ብየ አስባለሁ። በተለይ እንደ ተገልጋይ ሳስበው ዲጂታይዝድ በመሆኑ በወረቀት ሲሰጥ የነበረው የመንግስት መስሪያ ቤቶች ጉድለት ሌላ ችግር ተጨምሮበት ነው ያየሁ። ላስረዳ።

አንድ ተገልጋይ በወረቀት አገልግሎት ሲገለገል የሚያስፈልጉ ዶክመንቶችን ሲያሟላና ፈራሚዎች ከተገኙ አገልግሎቱን ያገኛል። ዲጂታይዜሽን የወረቀት አገልግሎት የሚያስፈልገውን ሁሉ ቢያሟሉ ሌሎች ተጨማሪ መሰናክሎች አሉት። “መብራት ጠፋ”፣ “ሲስተም አስቸገረ”፣ “ኢንተርኔት ደከመ” ወዘተ ከሚሉት በተጨማሪ የአገልግሎት ሰጪው የኮምፒውተር እውቀት ወሳኝ በመሆኑ ከወረቅት አገልግሎት በረዘመ እንጂ ባጠረ ጊዜ አገልግሎት አታገኙም።

ይህንን ስል የወረቀት አገልግሎት ከዲጂታይዝድ አገልግሎት ይሻላል እያልኩኝ እንዳልሆነ ይታሰብልኝ። የኔ ሃሳብ በወረቀት አገልግሎት ጊዜ ያስቸገሩንን ቢሮክራሲያዊ ችግሮች እስካልፈታን ድረስ ዲጂታይዝድ በማድረግ አገልግሎትን ማቀላጠፍ አይቻልም ባይ ነኝ። ‘ፈራሚ’ በስራ ሰዓቱ የማይገኝ ከሆነ አገልግሎቱ ሊቀላጠፍ አይችልም። በርካታ ‘ፈራሚዎች’ የሚጠበቁበት ከሆነ አገልግሎቱ ሊፋጠን አይችልም። ለአገልግሎቱ የሚያስፈልጉት ዶክመንቶች “በጣም ብዙ” ሆነው ባለበት ሁኔታ አገልግሎት ሊቀላጠፍ አይችልም። የአሰራር እውቀት ጉድለት ያለባቸውን ሰራተኞች ይዘን ‘ዲጂታይዝድ’ ብናደርገውም አገልግሎቱ ሊቀላጠፍ አይችልም።

በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ በወረቀት አገልግሎት ላይ ያሉ ጉድለቶች ላይ የዲጂታይዜሽን ጉድለቶችን ጨምረን አገልግሎታችን አይዘምንም። በቅድሚያ የቢሮክራሲ ችግሮቻችንን እንፍታ፣ ከዛም ዲጂታይዝድ እናድርግ እላለሁ፡፡

ገብረሕይወት ባይከዳኝ ዘብሔረ ቡልጋ

Sign Up For Daily Newsletter

Stay updated with our weekly newsletter. Subscribe now to never miss an update!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *