Home / ዜና ትንታኔ / ከማያረጅ ውበት እስከ ማይዝል ጉልበት

ከማያረጅ ውበት እስከ ማይዝል ጉልበት

ከዘፍጥረት በፊት ለዘመናት በብላሽ ባዕዳንን ሲያረሰርስ፣ ከትናንት ዛሬ አገሩን ሊያለማ ይዞት የሚዞረውን ግንድ ማደሪያ ሊሰራበት የችል የሆንን በሚል የተናፈቁ የዘለዓለም ዓመታት፡፡ ዓባይ፣ ግዮን፣ናይል፣ ማሃስ፣ አጉ፤ ስመ በዙው እና አይበገሬው ከገነት የፈለቀው ጅረት ከስከላ እስከ ሜዲትራንያን የተሸመነ ፈትል፡፡

‹‹የናይል ወንዝ በዓለም ላይ ካሉ ውብ ወንዞች አንዱ ነው፤ ምናልባትም በቸኛው ነው ማለት የቻላል፡፡ እንደዚህ ያለ ወንዝ ከባህል እና ወግ ጋር የተጋመደ የለም፡፡ ያለ ናይል ወንዝ ግብጽ የለችም፣ ፈርኦኖች አይኖሩም የግብጽ ፒራሚዶችም አይኖሩም››፡፡ ይህ የአገር አሳሹ እና ጂኦፊዚስቱ የፓስኳሌ ስኳቱሮ ምስክርነት ነው፡፡ ይህ አገር አሳሽ ከሰከላ ተነስቶ በአነስተኛ ጀልባ እና መቅዘፊያ ሜዲትራንያን ድረስ ቀዝፏል፡፡ ያመነው ዓባይ አልበላውም፣ በድፍረት ወደ መኖሪያቸው የሄደባቸው አዞዎች እና ጉማሬዎች እምብዛም አልተተናኮሉትም፡፡ ይህን ጀብድም ለኹለት ጊዜ አድርጎታል፡፡ ከ3000 በላይ ማይሎችን ነጉዷል አራት ወራትንም ጥራኝ ጫካው፣ ጥራኝ ደኑ ብሎ ከራርሟል፡፡

ይህ ሱዳንን ያቆመ፣ ግብጽን ያጠጣ መነሻውን ግን ከተረት እና ከግጥም በዘለለ ተሩፋቱን ያልሰጠው ክረምት ከበጋ ኮብላዩ ወንዝ አገሩ ላይ ሊገማሸር ልጓም ተበጅቶለታል፡፡ ከሺ ዘመናት በላይ የሚረዝሙ አስራ አራት ዓመታትን አልፍቷል፡፡ እኛ ባንችል መጪው ትውልድ ይገድበዋል ተብሎ በአጼ ኃይለሥላሴ የተዛተበት ውሃ አሁን አገሩ ላይ ከፍተኛውን ሐይቅ ፈጠሮ የተረፈው እንደለመደው መኮብለሉን ተያይዞታል፡፡

‹‹ከተመኙ ላይቀር ወንዝነት መመኘት

አገርን ሳይለቁ ሰው አገር መገኘት›› እንዲል ባለቀኔው አገሩ ላይ ሐይቅ ሆኖ አሁንም በረከቱን ላስለመዳቸው ሚልዮኖች የደንቡን ሊያደርስ ሰው አገር ይገኛል፡፡

ከ14 ዓመታት በፊት በወርሃ መጋቢት/2003 የያኔው የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ በድብቅ ሲመክሩበት የነበረውን እና ‹‹ፕሮጄክት ኤክስ›› ብለው ይዘውት የነበረውን አገራዊ፣ ቀጠናዊ በሎም አህጉራዊ የጂኦፖለቲካ ምህዋርን የሚዘውረውን ይህንኑን ግድብ ለሕዝብ ይፋ አደረጉት፡፡

 

‹‹በወንዙ የመጠቀም መብታችንን እንዲሁም ከወንዙም እንዳንገለገል የሚገታን ምንም አይነት ኃይል አይኖርም›› ሲሉም በኢትዮጵዊነት ወኔ እና በመሪነት ቆራጥነት አስታወቁ፡፡ ከዛማ ምን ይጠየቃል፤ ዓባይን ያህል ኮብላይ የአገር ሃብት ተይዞ የለም በገላጋይ፡፡ ‹‹አባይ ነጋ ጠባ ላቡን ያፈሰዋል››፣ ‹‹እንጉረጉሮ ይብቃ›› ተባለ፡፡ መድረኮች ዓባይን ሰበኩ፣ አንደበቶች ግድቡን ለፈፉ፤ ከሊቅ እስከደቂቅ ይህን ታላቅ አገራዊ ፕሮጄክት በእኔነት ቁጭት ተረባረበበት፡፡

ታዲያ እዚህ ላይ አንድ ትሁት እና ሰርቶ የሚደክም የማይመስል ጎልማሳ፤ ዓባይ ካልተገደበ ጺሜንም አልላጭም ያለ የመሰለ፣ ከዓባይ ጋር ጉባ ላይ የቆረበ የበረሃው መናኝ ኢንጅነር ስመኘውን ማንሳት የግድ ይሆናል፡፡ ቅርብ የወላጅ ክትትል የሚያስፈልጋቸውን ልጆቹን ለብቻቸው ትቶ ውሎ እና አዳሩ በዛ ሐሩር ጉባ ከሆነ ከራርሟል፡፡ ፋታ የሌለውን የስልክ ጥሪውን በትህትና ከማስተናገድ ባለፈ የአገርን ኃላፊነት በፊት መስመር እየመራ ሲባዝን ውሎ ያድራል፡፡

ገጠመኝ ከስመኘው ጋር

ዓመተ ምህረቱን በውል በማላስታውሰው የበጋ ወራት በሒልተን ሆቴል የመኪና ማቆሚያ ስፍራ ላይ ቆሜያለሁ፡፡ አንድ ቶዮታ ላንድክሩዘር ቪ8 ተሽከርካሪ የሆቴሉ ደንበኞች ተሽከርካሪዎቻቸውን ከሚያቆሙበት ስፍራ በተለዬ ስፍራ ላይ ቁሟል፡፡ በዚህ ስፍራ ላይ መቆሙ ብቻም ሳይሆን ተሽክርካሪውን ሙሉ በሙሉ ቀለሙን ሊቀይር በሚችል ሁኔታ በጭቃ መሸፈኑ ነው ትኩረቴን የሳበው፡፡ ለወትሮው ሽቷቸው ከግቢ ውጪ ጀምሮ አካባቢውን የሚያውደው ተሽከርካሪዎች በሚርመሰመሱበት የሒልተን ሆቴል ይህ ተሽከርካሪ መቼም ጎብኚዎችን ከመስክ አምጥቶ በቀጥታ እዚሁ አሳርፏቸው እንጂ ሌላ የማን ቢሆን ነው? ስል ራሴን ጠይቄያለሁ፡፡

በዙም ሳይቆይ ጅንስ ሱሪ ነጣ ባለ ሸሚዝ የለበሰ፣ ጫማው እንደነገሩ የተጠረገ፣ ከቆዳ የተሰራ ጥቁር ቦርሳ የያዘ እና ጸጉሩ በሚገባ ያልተበጠረ ወይም የተበጠረ ያልመሰለኝ አንድ ሰው በብዙ ሰዎች ታጅቦ ከሒልተን ውስጠኛው ክፍል ሲወጣ አየሁት፡፡ ራሱ ነው! አዎ ስመኘው ነው፡፡ ኹለት ሰዎችን በትክክል ያዋራቸዋል፣ ይመልስላቸዋል፣ ሌሎችን በጥቅሻም በፈገግታም ይዟቸዋል፡፡ ፈጠን ፈጠን ብለው ይራመዱና ምላሽ ለመስጠት ሲቆም የሚከተሉት በሙሉ ይቆማሉ፡፡

የመውጫውን ኮሪደር ጨርሰው ወደዛ ጭቃማ ላንድከሩዘር ሲያመሩ ነው የእርሱ ተሽከርካሪ መሆኑ የገባኝ፡፡ ምን እንደነካኝ አላውቅም፡፡ በፍጥነት ተወነጨፍኩ እና አጠገቡ ደረስኩ፡፡ ‹‹ኢንጅነር ስመኘው›› አልኩ ከከበባው ልቆ በሚሰማ ድምጽ፡፡ ስመኘውም የከበቡትም ዞረው አፈጠጡበኝ፡፡ ይሄ እድል እንዲያልፈኝ አልፈልግም ፎቶ እንነሳ አልኩት፡፡ ፈገግታውን ሳይቀንስ ‹‹አሁን ይመቻል ብለህ ነው? እንደምታየው እኮ ነው›› ሲል ምላሽ ሰጠኝ፡፡ ምላሹ አላረካኝም ወይም ራስ ወዳድ ነበርኩ መሰለኝ ፎቶ መነሳት እንዳለብን ወተወትኩ፡፡ እንዲያው ጥያቄውን ማን ደፈሮ ይጠይቅ ሲሉ የነበሩ በሚመስል አኳኋን ያ ሁሉ ከበባ ወዲያው ወደ ፎቶ መነሳት ውክቢያ ተሸጋገረ፡፡ የመጀመሪያውም የመጨረሻውም ስመኘውን በቅርበት ያገኘሁበት አጋጣሚ ይህ ነበር፡፡

ይህን የመሰለ ባለብዙ ጠላት ግድብን እየመራ እንዴት በእኔ በአንድ ተራ ሰው መገኘት ይችላል? እንዴት ጠባቂ እንኳን አይመደብለትም? አይነት ጥያቄዎች ሲመላለሱብኝ ሰንብተው ነበር በወቅቱ፡፡

 

ከጅማሮው ከ3 ቢልዮን ዩሮ በላይ ወይም በወቅቱ ምንዛሪ ከ87 ቢልዮን ብር በላይ በጀት የተያዘለት የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ከ14 ዓመታት በኋላ ሲጠናቀቅ ግን በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብቻ 223 ቢልዮን ብር የወጣበት እና ከህዝብ የተሰበሰበ 10 ቢልዮን ብር በድምሩ ወደ 233 ቢልዮን ብር ወጪ እንደተደረገበት በመንግስት ሪፖርት ተደርጓል፡፡ ሙስና፣ የግንባታው መጓተት እና እሱንም ተከትሎ የሚታየው የግንባታ ዕቃዎች ዋጋ መወደድ፣ የገንቢው ድርጅት ከዚሁ ጋር ተያይዞ በርካታ ሚልዮኖችን በካሳ መልክ መጠየቁ እና በርካታ ተያያዥ ጉዳች የወጪው መጨመር ምክንያት ተደርገው ይወሰዳሉ፡፡

ከመለስ እስከ ኃይለማርያም

የዚህ ግድብ ጀማሪ እና ወላጅ አባት መለስ ዜናዊ ለመሆናቸው ትውልድ የሚዘክረው እና ታሪክም የሚያወሳው ሃቅ ነው፡፡ በትውልድ ቅብብሎሽ የሚፈጸሙት እንዲህ ያሉ አገራዊ ፕሮጄክቶች ጀማሪውን ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊን ከአንድ ዓመት በላይ ሊመሩት እና መመሪያ ሊሰጡበት አልቻሉም፡፡ በ2004 ክረምት በወርሃ ሐምሌ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፡፡ ምንም እንኳን ከግድቡ መሰረት ድንጋይ መቀመጥ በኋላ አንድ ዓመት ብቻ በህይወት ቢቆዩም አስቀድሞ የነበረው ውጣ ውረድ ግን በእጅጉ ከፍተኛ የአርበኝነት ስራ የተሰራበት እና እንዲያውም በዘመናዊት ኢትዮጵያ በደማቅ የሚጻፍ ነው ይላሉ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ባልደረቦች፡፡ ‹‹ግብጽ ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ ግድብ ከመገንባት ልታግዳት አትችልም›› የሚለው ንግግራቸው የካይሮን ሹመኞች በቁጣ ያበገነ እና ምንም ማድረግ አለመቻል ምን ያህል እንደሚያምም የቀመሱበት ንግግር ነው፡፡

የመለስ ዜናዊ ጠንካራው የአመራር ልህቀት እና በተለይም ደግሞ ዓባይን በሚመለከት ከዓለም አቀፍ በተለይም ደግሞ ከግብጽ የሚሰነዘረውን ዘርፈ ብዙ ጫና በመመከት ረገድ የተተኪው ኃይለማርያም ደሳለኝ ሚና በጉልህ የሚጻፍ ነው፡፡ የዲፐሎማሲው ጫና እና ፈትጊያዎች ኃይለማርያም ደሳለኝ በለጋ የስልጣን ዘመናቸው ከተፈተኑባቸው አንጓዎች ቀዳሚዎች እንደነበሩ ወቅቱን የትናንት ያህል ሳያዛንፉ የሚያስታውሱ የወቅቱ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ባልደረባ የነበሩ ሰዎች ለዚህ ጽሑፍ ግብዓት እንዲሆን ይናገራሉ፡፡ በፈረንጆች 2015 የካርቱም ስምምነት በመባል የሚታወቀውን ውል ሲፈረም ጠ/ሚር ኃይለማርያም ደሳለኝ በአገር ወዳድነት እና በፍጹም የመሪነት ችሎታ ነበር የተፋለሙት ይላሉ አስተያየት ሰጪዎች፡፡

 

‹‹ከለውጡ ማግስት››- እስክ ምረቃ (ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ)

በዓባይ ወንዝ እና በግድቡ ጉዳይ በካይሮ ተገኝቶ በይፋ ውይይት እና ቃለ መሐላ የገባ መሪ ከጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ ውጭ አይኖርም፡፡ እነዚህን መሐላዎች እና የቃል ውሎች ወደ ጎን አድርገን ጠ/ሚር ዐብይ አህመድ ኢትዮጵያ በጽኑ በተፈተነችበት ወቅት በተለይም ደግሞ የሕዳሴው ግድብ ጉዳይ ዓለምን በሰፊው ባንቀሳቀሰበት ወቅት ኢንጅነር ሰለሺ በቀለን እና ገዱ አንዳርጋቸውን ግራ እና ቀኝ አሰልፈው መዝመታቸው እና ከድል ማግስት ግድቡን ለምረቃ ማብቃታቸው የግድቡን ፈጻሚነት የታሪክ ዕድል እና አጋጣሚ ያድላቸዋል፡፡

 

ከላይ በገጠመኝ ያገኘሁት ብኩን ኢንጅነር ታዲያ የወቅቱ ጠ/ሚር ዐብይ አህመድ ወደ ስልጣን በመጡ በጥቂት ጊዜያት ውስጥ በዛው ከነጭቃው ባየሁት መኪናቸው ውስጥ ሞተው ተገኙ፡፡ ራሳቸውን አጠፉ ይባል እንጂ በሰው ዕጅ መገደላቸው ሕዝብ ፍትህ የሚጠይቅባቸው ንጹህ የህዝብ አገልጋይ ነበሩ፡፡

ታላቁ የህዳሴው ግድብ ዛሬ ጷግሜ 4/2017 በተወለደ በ14ኛ ዓመቱ ለምረቃ ይበቃል፡፡ ሕዝብን በደስታ ያስተሳሰረ፣ ትናንትን፣ ዛሬን እና ነገን በተስፋ ሸምኖ ያስተሳሰረ፡፡ የአንድነት ምልክት፣ የአልበገር ባይነት ተምሳሌት የነገዋ ኢትዮጵያ የማዕዘን ድንጋይ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ!!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *