Home / ዜና ትንታኔ / ቆመው የገመዱት ሰብዓዊነት፤ ሞተው ፍሬውን አይተዋል!

ቆመው የገመዱት ሰብዓዊነት፤ ሞተው ፍሬውን አይተዋል!

ቆመው የገመዱት ሰብዓዊነት፤ ሞተው ፍሬውን አይተዋል!

የተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ ሞት ኢትዮጵያንን ከሰሜን እሰከ ደቡብ፣ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ ያለ ሃይማኖት ልዩነት በሰውነት በአንድ ጎራ ያሰለፈ ታሪክ ሆኖ ተመዝግቧል። ‘ሰው ሁኑ፣ ሰውነት ከሁሉ ይበልጣል’ በሚለው ንግግራቸና በሰው ልጆች ላይ የሚፈጸም ግፍን በአደባባይ በመኮንን የሚታወቁ ሙፍቲ ሞት ኢትዮጵያዊያንን ያለ ልዩነት በአንድነት አሰልፏል። ብዙዎች ‘የሀገር ዋርካ፣ የሰብዓዊነት ውሃ ልክ፣ የሰውነት ምሳሌ፣ ሀገር ወዳዱ መካሪ፣ የእውነት ድምጽ…’ እያሉ ከልብ በመነጨ ሐዘን ሙፍቲን ከሞቱም በኋላ የጋራ ምልክት አድርገዋቸው። እኛም የ’ሰውነት ይቀድማል’ አቀንቃኙን የሀገር ዋርካ በተመጠነ የህይወት ታሪክ ዳሰሳ የዝግጅት ክፍላችን ሊዘክራቸው፤ ህያው ስራቸውን ያወሳል፡፡

ሐጂ ዑመር ኢድሪስ ማን ናቸው?

 

ሙፍቲ የተወለዱት በያኔው ወሎ ጠቅላይ ግዛት በአሁኑ አማራ ክልል ለጋምቦ ወረዳ ልዩ ስሙ ገነቴ በሚባል አካባቢ ሲሆን የትውልድ ዘመናቸው ደግማ ግንቦት 21/1929 ። ገና በለጋ ዕድሜያቸው የእስልምና አስተምህሮ የመቅሰም ፍላጎት አድሮባቸው የሃይማኖት ትምህርት ተከታትለዋል። ሙፍቲ የስማቸው መጠሪያ እስከመሆን በደረሰችው ገነቴ በልጅነታቸው የጀመሩት የእስልምና ትምህርት የተሻለ እውቀት ፍለጋ ወደ አዲስ አበባ አክንፏቸዋል።

ከ50 ዓመታት በፊት ወደ አዲስ አበባ የተጓዙት ኡስታዛቸውን ወይም የእስልምና መምህር ፍለጋ ነበር። ትምህርት ፍለጋ ከወሎ አዲስ አበባ የዘለቁት ሙፍቲ የሃይማኖቱ እውቀት ስለነበራው ብዙም ሳይቆዩ፣ በአንዋር መስጂድ በኡስታዝነት ተመድበው አስተምረዋል።

ማልዶ የተዋደዳቸው ቀናነት እና ተወዳጅነት ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ በአዲስ አበባ ቆይታቸው በእምነቱ ተከታዮች እና በዙሪያቸው ባሉ ሰዎች ቀቡልነት ወደ ፊት እንዲመጡም ሆነዋል፡፡ በተለያዩ የእስልምና ሃይማኖት አደረጃጀቶችን በመመስረትና በመምራት የእምነቱ ተከታዮች አሰባሳቢ ተቋማትን በመገንባትም ይታወሳሉ።

በደርግ ዘመነ መንግሥት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮችን ከመሰረቱት ሰዎች መካከል አንዱ እንደነበሩ ታሪካቸው ያስረዳል። ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ ከ2011 መጋቢት ወር እስከ ግንቦት 2014 ድረስ የኢትዮጵያ እስልምና ጠቅላይ ምክር ቤትን በፕሬዝዳንትነት መርተዋል። ሙፍቲ መጅሊሱን በመሩባቸው አራት ዓመታት ከእስልምና እምነት ተከታዮች በተጨማሪ በሌሎች አማኞች ዘንድም ከፍተኛ ተቀባይነት ነበራቸው። ከእስልምና ተከታዮች በተጨማሪ ተቀባይነት ያገኙት ደግሞ ከሃይማኖት በፊት “ሰውነት ይቀድማል” በሚለው መርሃቸው ነው። ይህም ደግሞ ከሊቅ እስከ ደቂቅ ሳይገደድ ላነባው ደግነታቸውን አሰቦ መለየታቸው ያስለቀሰው ወፍ ሰማይ ሕያው ምስክር ነው፡፡

ሰው መሆንን መርህ ያደረጉት እኚህ አባት በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የተፈጠሩ አለመግባባቶችን እና ግጭቶችን በመፍታት ይታወቃሉ። የመጅሊሱ መሪ በነበሩባቸው ዓመታት ከወለጋ እስከ መተከል በንጹሃን ዜጎች ላይ በማንነት ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ሲፈጸም፣ ያለ መወላወል በትረ መኮንን ሳያስጎነብሳቸው፣ የሹማምንት ግልምጫ ሳያሸብራቸው ለእውነት ቆመው ጥቃቶችን ሳያወግዙ የቀሩበት ጊዜ አልነበረም።

 

ደርባባ መንፈሳዊነትን ከቁጥብ አንደበት ጋር የተዋሃዱት ሐጂ የመጨረሻ የአመራርነት ዘመናቸው ኃይል በተቀላቀለበትና በወቅቱ ‘መፈንቅለ መጅሊስ’ ተብሎ የተሰየመው ድርጊት እንዲሰናበቱ ሆኗል፡፡ የህይወታቸው የመጨረሻ ምዕራፍም በትካዜ እንዲያልፍ ማድረጉ በጣፋጩ አንደበታቸው ከትህትና ሳይጎድሉ መናገራቸው ይታወሳል። ሙፍቲ ከመጅሊሱ መሪነታቸው የተነሱበት መንገድ ወከባ የታከለበት ክስተት እንደነበር ይታወሳል።

ሙፍቲ በወከባ ከመጅልሱ ከተነሱ በኋላ በሰጡት አንድ ቃለ መጠይቅ በህይወታቸው ያዘኑበት ወቀት እንደነበር ተናግረዋል። በህይወት ዘመናቸው ስላዘኑበት አጋጣሚ ተጠይቀው “በህይቴ ያዘንኩት አሁን ነው” በማለት ነበር የመለሱት።

ከዚያ በኋኃ አብዛኛውኝ ህይወታቸውን ከአደባባይ ተሰውረው ለማሳለፍ ተገደዋል። ለወትሮው በዜጎችን ላይ የሚፈጸሙ ግፎችን በአደባባይ በመቃወምና ሰብዓዋነትን በመስበክ የሚታወቁት ሙፍቲ ታሪካዊ አሻራቸውን ጥለው አልፈዋል።

የ “ሰውነት ይቀድማል” አቀንቃኙ መፍቲ መጅሊሱን በመሩባቸው ዓመታት ያሳዩት ለሀገርና ሕዝብ አንድነት መቆርቆር የብዙዎችን ቀልብ ስቧል። የሰብዓዊነት ተምሳሌትነታቸው በሞታቸው ይበልጥ ጎልቶ ወጥቶ ያለ ሃይማኖት ልዩነት ኢትዮጵያን ጥልቅ ሐዘናቸውን ገልጸዋል። ሙፍቲ ቆመው የገመዱት አንደነት እና ሰብዓዊነት በሞታቸው ታየ፡፡ ብሔር፣ ኃይማኖት፣ ጾታ ሳይለይ በእንባ የሸኛቸው ሕዝብ ከእሳቸው መለየት በላይ አስታራቂ ማጣቱ ያበሰለሰለው ይመስላል፡፡

ሙፍቲ “ሰው መሆን ይቀድማል” በሚለው መርሃቸው በሃይማኖት ልዩነት መካከል የሰብዓዊነት ድልድይ መኖሩን በተግባር አስተምረው አልፈዋል። አገርን ሰናስብ የእኚህ ክቡር ሰው መለየት አንድ እንኳን የሚያስማማ ሽማግሌ ለማግኘት ለምትማስነው አገር ምን ያህል እንደሚያጎድል ቀናት ሳይቆጠሩ የምናየው የሆናል፡፡

የ89ዓመቱ ትሁት አባት ሲወዷት የኖሩት ኢትዮጵያ ሰንደቋን ተውበውበት አሸልበዋል!!

 

Sign Up For Daily Newsletter

Stay updated with our weekly newsletter. Subscribe now to never miss an update!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *