በትግራይ ርዕሰ መዲና የታጠቁ ኃይል አባላት የክልሉን ጊዜያዊ አስተዳደርን ጽሕፈት ቤት ሕንጻ በዛሬው ዕለት ከበባ መፈጸማቸውን የሆርን ፍሪኩዮንሲ ምንጮች ገልጸዋል።
ምንጮቹ እንዳስታወቁት፣ የዚህ ያልተጠበቀ ክስተት ዋነኛ ምክንያት በአብዛኛው ሰዎች ዘንድ እንደሚነገረው ደመወዝ ዘገየብን የሚል ጥያቄ ሳይሆን፣ በታጥቁ በኃይል አባላት መካከል በተፈጠረ የኃይል ፉክክር የተነሳ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል
የፖለቲካው ክንፍ በዶ/ር ደብረጽዮን ገብረ ሚካኤል እና በሞንጆሪኖ ይመራሉ የተባሉት እና አርሚ 31 የተሰኘው ታጣቂ ቡድን ከትግራይ የተለያዩ አካባቢዎች ተነስተው በጊዜያዊ አስተዳደሩ ሕንጻ ላይ ከበባ ያደረጉበት ምክንያት፣ ከዚህ ቀደም የአቶ ጌታቸው ረዳ ደጋፊዎች ናቸው የተባሉ ታጣቂዎች በትጥቅ ታግዘው ያደረጉትን እንቅስቃሴ በማንሳት “እኛም አቅማችንን እናሳያለን” በሚል ተነሳስተው መሆኑን ምንጮቹ አመልክተዋል።
ታጣቂዎቹ የጊዜያዊ አስተዳደሩን ሕንጻ ከበባ ውስጥ ሲያስገቡ የተለያዩ የግል እና የቡድን የጦር መሳሪያዎችን ይዘው መታየታቸውን የሆርን ፍሪኩዮንሲ አይን እማኞች ገልጸዋል።
እነዚህ ታጣቂዎች ከዛሬ ጠዋት 1፡00 ሰዓት ጀምሮ ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ድረስ ከበባ እንዳደረጉ ሲሆን፣ የክልሉ ከፍተኛ ባለስልጣናት እንዲያነጋግሯቸው ብቻ እንደሚፈልጉ እየገለጹ ነው። ይህ ጥረታቸው የፖለቲካዊ ውጥረትን እና የኃይል ሚዛንን የማሳየት ፍላጎት እንጂ የደመወዝ ክፍያ ጥያቄ እንዳልሆነ ተጠቁሟል። ከዚሁ ጋር ተያይዞም ሆርን ፍሪኩዌንሲ ያነጋገራቸው የትግራይ ቴሌቪዥን ስራተኞችም ሕንጻውን ለቀው እንዲወጡ እንደተደረጉም አስታውቀዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ከበባ ካደረጉት ታጣቂዎች በተጨማሪ፣ ከክልሉ የተለያዩ አካባቢዎችም ሌሎች ታጣቂዎች ወደ ከተማዋ እየገቡ መሆኑ ተገልጿል። ታጣቂዎቹ ከበባ ማድረግ ከጀመሩበት ጊዜ ወዲህ በክልሉ የተሽከርካሪ እንቅስቃሴ መቆሙን ጨምሮ በአስተዳደሩ ዋና መሥሪያ ቤት አካባቢ ያሉ ባንኮች፣ የመንግስት እና የግል ተቋማት ዝግ መሆናቸው ታውቋል።
ከበባው የፈጠረው ውጥረት ባለበት ከሰዓታት በፊት የከባድ መሳሪያ ድምጽ መስማታቸውንም ምንጮች ለዝግጅት ክፍላችን አስታውቀዋል፡፡










