Home / ፖለቲካ / በሕወሓት እና በትግራይ የሰላም ኃይሎች መካከል በአፋር ውጊያ ተቀሰቀሰ

በሕወሓት እና በትግራይ የሰላም ኃይሎች መካከል በአፋር ውጊያ ተቀሰቀሰ

የህወሓት እና ራሱን ሐራ መሬት (የትግራይ ሰላም ኃይል) በሚል የሚጠራው ቡድን መካከል በትግራይ እና አፋር አዋሳኝ ስፍራዎች ላይ ውጊያ መግጠማቸውን ሆርን ፍሪኩዌንሲ ከአካባቢው ምንጮቹ ሰምቷል።

በሁለቱ የትግራይ ኃይሎች መካከል ባለፉት ሦስት ቀናት አልፎ አልፍ የተኩስ ልውውጦች የተደረጉ ሲሆን፣ ጥቅም 26/2018 ዓ.ም ምሽት 1:00 ገደማ ጠንከር ያለ ውጊያው ገጥመዋል ተብሏል። በህወሓት በኩል በከባድ መሳሪያ የተደገፈ ጥቃት አፋር ክልል በሰፈረው ሓራ መሬት ኃይሎች ላይ ምሽቱን መክፈቱን ምንጮች ገልጸዋል።

ሰሞነኛው የተኩስ ልውውጥ ወደ ውጊያ የተሸጋገረው የህወሓት ኃይሎች ወደ አፋር ክልል ዘልቀው በመግባት ጥቃት መክፈታቸውን ተከትሎ ነው ተብሏል።

ውጊያው የተቀሰቀሰው በራያ በኩል በአፋር ክልል ውስጥ መሆኑ ተጠቁሟል። የህወሓት ኃይሎች በከፈቱት ጥቃት ወደ አፋር ክልል ዘልቀው የተወሰኑ ቀበሌዎችን መቆጣጠራቸው ታውቋል።

የአፋር ክልልል መንግሥት ህወሓት ወሰን ጥሶ ጥቃት እንደከፈተበት አስታውቋል። የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ በጉዳዩ ላይ ባወጣው መግለጫ ህወሓት ወሰን ጥሶ በመግባት ስድስት መንደሮችን በጉልበት መቆጣጠሩን አረጋግጧል።

ክልሉ በመግለጫው ህወሓት “ንጹሃንን በሞርታርና በዙ-23 በመደብደብ የተለመደውን የሽብር ተግባሩን በግልጽ ጀምሯል” ብሏል። በክልሉ በዞን ሁለት በመጋሌ ወረዳ ቶንሳ ቀበሌ ዋራዓ እና ሚልኪ በሚባሉ ልዩ አካባቢዎች ወሰን ተሻግሮ በመግባት ከምሽቱ አንድ ሰአት አካባቢ፣ በንጹሐን የአፋር አርብቶ-አደሮች ላይ የከባድ መሳሪያ ተኩስ በመክፈት የፕሪቶሪያ ስምምነትን በግጭት አዋጅ በግልጽ አፍርሷል ሲልም አክሏል።

ክልሉ ህወሓት “ከድርጊቱ በአስቸኳይ ካልተቆጠበ” የዜጎች ደህንነትና ወሰኑን ለማስጠበቅ፣ እንዲሁም ራስን ከጥቃት የመከላከል እርምጃ እንደሚወስድ አስጠንቅቋል።

የህወሓት ኃይሎች ቶንሳ ተብሎ በሚጠራው የአፋር አካባቢ የአፋር ሽማግሌዎች እንዲመለሱ ቢጠይቋቸውም፣ ግጭቱን ገፍተውበታል ተብሏል።

Sign Up For Daily Newsletter

Stay updated with our weekly newsletter. Subscribe now to never miss an update!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *