Home / ፖለቲካ / የኦሮሞ ነጻነት ጦር መሪ ጃል መሮ ለድርድር በቀይ መስቀል ሄሊኮፕተር ተወሰዱ

የኦሮሞ ነጻነት ጦር መሪ ጃል መሮ ለድርድር በቀይ መስቀል ሄሊኮፕተር ተወሰዱ

በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የትጥቅ ትግል እያደረገ የሚገኘው የኦሮሞ ነጻነት ጦር (OLA) ከፍተኛ መሪ ጃል መሮ ከፌደራል መንግሥት ጋር ለሚደረገው ከፍተኛ የሰላም ድርድር በዛሬው ዕለት ከገዢ ቀጠናቸው ወደ አልታወቀ ስፍራ መወሰዳቸው ተሰማ።

ምንጮቻችን ለሆርን ፍሪኩዮንሲ እንደገለጹት፣ ጃል መሮ ከታማኝ አባሎቻቸው ጋር በመሆን፣ በአለም አቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ አደራዳሪነትና የደኅንነት ዋስትና ሰጪነት፣ በልዩ ሄሊኮፕተር አማካኝነት ከአንድ ሚስጥራዊ ስፍራ ተነስተው ለድርድር ወደተዘጋጀው ስፍራ ተጉዘዋል ብለዋል። ምናልባትም ከጎረቤት አገራት ኬንያ ወይም ከዚህ ቀደም በተደረገበት ታንዛንያ ሊሆን እንደሚችልም ተገምቷል፡፡

የቀይ መስቀል ኮሚቴ (ICRC) በጦርነት ቀጠናዎች መካከል የገለልተኝነት ሚናውና የመንቀሳቀስ ነጻነቱ፣ የሁለቱም ወገኖች መሪዎች በአስተማማኝ ሁኔታ ተገናኝተው እንዲመክሩ ትልቅ ድጋፍ እንደሰጠ ታውቋል።

የጃል መሮ ወደ ድርድር መድረክ መምጣት፣ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ባሉ የፖለቲካ እና የደኅንነት ችግሮች ላይ ሰፋ ያለ ውይይት ለማድረግ በር መክፈቱ እየተገለጸ ነው።

ከዚህ ቀደም በኦሮሞ ነጻነት ጦር እና የፌደራል መንግስት መካከል በታንዛንያ ድርድር ተካሂዶ እንደነበር የሚታወቅ ሲሆን ድርድሩ ያለ ውጤት መጠናቀቁም ይታወሳል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ከዚህ በፊት በተለያዩ አጋጣሚዎች የሰላም ጥሪ ሲያቀርብ የነበረ ሲሆን፣ የዛሬው ክስተት የሁለቱ አካላት ለሰላም ያላቸውን ቁርጠኝነት በተግባር የሚያሳይ ነው። በተፋላሚ ወገኖች በኩል የመንግስት የሰላም ጥሪ እውነተኛ አይደለም እየተባለ ምላሽ ሲሰጥበት መቆየቱም የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡

ሆርን ፍሪኩዮንሲ የሰላም ድርድሩን ሂደት በቅርበት እየተከታተለ ዝርዝር መረጃዎችን ለታዳሚዎች የሚያደርስ ይሆናል።

Sign Up For Daily Newsletter

Stay updated with our weekly newsletter. Subscribe now to never miss an update!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *