Home / ፖለቲካ / የጣና ፎረም ከሦስት ዓመታት በኋላ ሊካሄድ ነው

የጣና ፎረም ከሦስት ዓመታት በኋላ ሊካሄድ ነው

ላለፉት ሦስት ዓመታት በአማራ ክልል ባለው የጸጥታ ስጋት ምክንያት ላልተወሰኑ ጊዜያት ሲተላለፍ የነበረው የጣና ፎረም 11ኛው ዓመታዊ ስብሰባ በባህር ዳር ሊካሄድ ነው፡፡

በየዓመቱ በአፍሪቃ የሰላም እና ደኅንነት ዙሪያ መሪዎች እና የዘርፉ ምሁራን የሚመክሩበት የጣና ፎረም በመጪው ዓርብ ጥቅምት 14/2018 በባህር ዳር ይጀመራል፡፡

10ኛውን ዓመታዊ ጉባኤ ከሦስት ዓመታት በፊት በባህር ዳር ካካሄደ በኋላ ከጸጥታ ጋር በተገናኘ ላለፉት ዓመታት ሳይከናወን መቆየቱ የሚታውስ ሲሆን፤ ከሦስት ዓመታት በኋላ ዘንድሮ 11ኛው ዙር ስብሰባ ‹‹Africa in an Evolving Global Order›› በሚል ሃሳብ ዙሪያ ይከናወናል፡፡

በስብሰባው ላይ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ እንዲሁም ሌሎች የአፍሪቃ አገራት መሪዎች እንደሚገኙበት ይጠበቃል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ከመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት እና የሰላም እና ደኅንነት ምሁራን በተጨማሪ የተለያዩ አገራት አምባሳደሮች እና የዲፐሎማት ማህበረሰብ አባላትም እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል፡፡

ጣና ፎረም በቀድሞው የአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ፕሬዘዳንት አንድሪያስ እሸቴ (ፕ/ር) እና የአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የሰላም እና ደኅንነት ጥናት ተቋም ዳይሬክተር የነበሩት ሙሉጌታ ገ/ሕይወት (ዶ/ር) እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ርብርብ ዕውን እንደሆነ ይነገራል፡፡

ላለፉት ዓመታትም የአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የሰላም እና ደኅንነት ጥናት ተቋም ዝግጅቱን በዋናነት ሲመራው መቆየቱ የሚታወስ ነው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *