Home / ፖለቲካ / ኤርትራ እና ህወሓት የፋኖ ኃይሎችን በመደገፍ በመንግሥታቱ ድርጅት ተከሰሱ

ኤርትራ እና ህወሓት የፋኖ ኃይሎችን በመደገፍ በመንግሥታቱ ድርጅት ተከሰሱ

የኢትዮጵያ መንግሥት ከፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት በተቃራኒ ‘ጽምዶ’ በሚል ‘ጦርነት ለማወጅ’ ተባብረውብኛል ያላቸውን፣ ኤርትራ እና ህወሓትን የፋኖ ኃይሎችን እየደገፉ ነው በማለት ከሷል።

ኤርትራ እና ህወሓት የፋኖ ኃይሎችን በመደገፍ የተከሰሱት የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በጻፉት ደብዳቤ ነው። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ለመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ጸሐፊ ባቀረቡት አቤቱታ ኤርትራ ኢትዮጵያን በማተራመስ ላይ ተጠምዳለች በማለት ከሰዋል።

ኤርትራን እና ህወሓትን በኢትዮጵያ ላይ ‘ጦርነት’ ለማወጅ በማበር የከሰሰው መንግሥት፣ ትብብሩ በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱትን የፋኖ ኃይሎች እስከመደገፍ የዘለቀ ነው ብሏል። እንደ ማሳያም ባለፈዉ ሳምንት በሰሜን ወሎ ዞን ወልዲያ ከተማ ዙሪያ የፋኖ ኃይሎች የፈጸሙትን ጥቃት ላይ እርትራ እና ህወሓት እጃቸው እንዳለበተ በደብዳቤው ተገልጿል።

የፋኖ ኃይሎች መስከረም 16/2018 ዓ.ም በወልዲያ ከተማ ዙሪያ በፈጸሙት ጥቃት በመቶዎች የሚቆጠሩ የመንግሥት ኃይሎችን መማረካቸውን መግለጻቸው ይታወሳል። በምርኮ የያዟቸውን የመከላከያ ሰራዊት፣ የአማራ ክልል አድማ ብተና፣ ፖሊስና ሚሊሻዎችን በተንቀሳቃሽ ምስል ቀርጸው በማሰራጨት ቀይ መስቀል እንዲረከባቸውም ጠይቀዋል።

በዚሁ ከወትሮው ለየት ባለ ከባድ ውጊያ ላይ የኤርትራ እና ህወሓት የፋኖ ኃይሎችን በመምራት መሳተፋቸውን በደብዳቤው ተመላክቷል። በተለይም የህወሓት ወታደራዊ አዛዦች እና ተዋጊዎች የመንግሥት ኃይሎች በተማረኩበት ውጊያ በቀጥታ ተሳትፈዋልም ተብሏል።

ኢትዮጵያን ለማጥቃት ተባብረዋል የተባሉት ኤርትራ እና ህወሓት ለፋኖ ኃይሎችን በመምራት በወልዲያው ጥቃት ተሳትፈዋል ቢባልም፣ ጉዳዩ በገለልተኛ አካል የተረጋገጠ መረጃ የለም። የፋኖ ኃይሎች መሰል ጥቃቶችን በሁለት ዓመቱ ግጭት በተደጋጋሚ መፈጸማቸው የሚታወስ ሲሆን፣ በኤርትራ እና ህወሓት ይደገፋሉ የሚለው ክስ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጎልቶ እየተሰማ ነው።

የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትቴር ከወራት በፊት በተመሳሳይ ሁኔታ ለመንግሥታቱ ድርጅት በጻፈው ደብዳቤ ኤርትራን እንደ ፋኖ ያሉ ታጣቂ ኃይሎችን በመደገፍ መክሰሱ ይታወሳል።

ከኤርትራ ወገንም የማስታወቂያ ሚንስትሩ የማነ ገ/መስቀል በግል የኤክስ ገጻቸው በርካታ ኢትዮጵያን እና የኢትዮጵያን መንግስት እንዲሁም ገዢውን ፓርቲ ሲያንቋሽሹ ታይተዋል፡፡

Sign Up For Daily Newsletter

Stay updated with our weekly newsletter. Subscribe now to never miss an update!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *