Home / ቢዝነስ / በመቐለ ከተማ የተሞከረ ከባድ የባንክ ዘረፋ ከሸፈ

በመቐለ ከተማ የተሞከረ ከባድ የባንክ ዘረፋ ከሸፈ

በትግራይ ክልል መዲና መቐለ የታጠቁ ኃይሎች የኢትዮጵያን ንግድ ባንክ ለመዝረፍ ያደረጉት ሙከራ፤ ጥሬ ገንዘብ አስቀድሞ በመሸሹ ሙከራው ሳይሳካ መቅረቱን ምንጮች ለሆርን ፍሪኩዌንሲ ገለፁ

በከተማው ውስጥ የሕወሃት ታጣቂዎች ናቸው የተባሉ የታጠቁ ኃይሎች በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የኢትዮጵያን ንግድ ባንክ ቅርንጫፎችን በኃይል በመዝረፍ ጥሬ ገንዘብ ለመውሰድ ያደረጉት ሙከራ እንዳሰቡት ሳይሆን መቅረቱን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ዛሬ አመሻሽ 12፡00 ሰዓት ገደማ ጀምሮ የሕወሃት ታጣቂዎች የባንክ ቅርንጫፎች ውስጥ በመግባት ዝርፊያውን ያካሂዱ የነበረ ቢሆንም፣ ከተወሰነ የጥሬ ገንዘብ ውጪ ሊዘርፉ ያሰቡትን ያክል የገንዘብ ክምችት ማግኘት አለመቻላቸውን የከተማዋ ነዋሪዎች ለሆርን ፍሪኩዌንሲ ገልጸዋል።

መንግሥት ታጣቂዎቹ የዝርፊያ ድርጊት ሊያካሂዱ ይችላሉ በሚል ቀድሞ በመጠራጠሩ፣ በቅርንጫፎቹ ውስጥ የነበሩ ከፍተኛ የጥሬ ገንዘብ ክምችቶችን አስቀድሞ ወደ አስተማማኝ ቦታ በማሸሹ ምክንያት ታጣቂዎቹ ከፍተኛ ገንዘብ ሳይወስዱ መቅረታቸው ተገልጿል።

ይህም ታጣቂዎቹ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ የመውሰድ ዕቅዳቸውን እንዳያሳኩ አድርጓቸዋል ነው የተባለው። ነዋሪዎች እንደሚሉት፣ የታጣቂዎቹ ዋና ትኩረት የመንግሥት ባንክ ቅርንጫፎች ላይ ብቻ የነበረ ሲሆን፣ ከዚህ የዝርፊያ ድርጊት ውጭ በከተማዋ ሌላ ከፍተኛ የጸጥታ ችግር አልተፈጠረም።

መንግሥት በክልሉ የሚገኙ የገንዘብ ክምችቶችን አስቀድሞ እንዳሸሸ መገለጹን ተከትሎ፣ የትግራይ ክልል ነዋሪዎች ባንኮች በሚሰጡት አገልግሎት ላይ ከፍተኛ ችግር እንደገጠማቸው እና በክልሉ ከፍተኛ የጥሬ ገንዘብ እጥረት ተከስቶ መሰንበቱን መዘገባችን ይታወሳል፤ ይህም የዕለት ተዕለት የንግድና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ተፅእኖ አሳድሯል።

የተዘረፈው ገንዘብ ትክክለኛ መጠን እስካሁን አልተገለጸም።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *