ጠቅላላ ጉባኤውን እያደረገ የሚገኘው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በኢትዮጵያ ያለው የጸጥታ ሁኔታ በአሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ አስታውቋል።
በቃል አቀባዩ በኩል የተናገረው ተመድ ሁሉም ተፋላሚ ኃይሎች ከጦርነት እና ከመሳሪያ መማዘዝ በተለየ መልኩ ችግሮችን መፍታት እንደሚኖርባቸውም አሳስቧል። በተለይም ደግሞ በቅርቡ የተመሰረተውን ትብብር ለህልውና የተሰኘውን የአገር ውስጥ የተፋላሚ ኃይሎችን ጉዳይ በሚመለከት እና የተጠናከረውን የድሮን ጥቃት በመጥቀስ የጉዳዩን አሳሳቢነት አስታውቋል።
አዲስ በተፈጠረው የተፋላሚ ኃይሎች ትብብር ዙሪያ ተጨማሪ ማብራሪያዎችን ከመስጠት የተቆጠቡት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቃል አቀባይ ስቴፈን ጃሪክ የተባበሩት መንግስታት በአፍሪካ ህብረት መሪነት የሚደረገውን ውጥረትን መቀነስ ጥረት እና የፕሪቶሪያው ስምምነት አተገባበር ላይ ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።
ከቀናት በፊት በትግራይ ቴሌቪዥን አማካኝነት ለህዝብ ይፋ የተደረገው የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ኃይሎች ትብብር ለህልውና የተሰኘው ስብስብ ከመንግስት ዘንድ ይፋዊ ምላሽ ባይሰጥበትም በርካታ እርምጃዎች እየተወሰዱ እንደሆነ እና ከዚህም ውስጥ የትብብሩ መረጃ የተሰራጨበት የትግራይ ቴሌቪዥን በሚዲያ ባለስልጣኑ መታገዱ ይታወሳል።
በተጨማሪም በማህበራዊ ሚዲያ በኩል ሰፊ ማብራሪያ እንዲሁም ሙግት እያስተናገደ የሚገኘው ይህ ትብብር ይፋ ከተደረገበት ጊዜ ወዲህ ከፍተኛ እና የተጠኑ የድሮን ጥቃቶች በሕወሃት ኃይሎች ላይ መደረጉን ምንጮች አስታውቀዋል።
በ81ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያ በጠቅላይ ሚንስትሩ የምስራቅ አፍሪቃ ጉዳዮች አማካሪ ጌታቸው ረዳ እና በፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀስላሴ አማካኝነት ተወክላለች።












