ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ጋዝ ማውጣት መጀመሯን ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ አስታውቀዋል።
በሶማሌ ክልል የተገነባው የኦጋዴን ፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ ማውጫ የመጀመሪያ ዙር ግንባታ ተጠናቆ ተመርቋል። በዓመት 111 ሚሊዮን ሊትር የማምረት አቅም አለው ፕሮጀክት መጠናቀቁን ተከትሎ፣ ሁለተኛው ዙር ተጀምሯል ተብሏል።
በዓመት 1.33 ቢሊዮን ሊትር የማምረት አቅም እንደሚኖረው የሚጠበቀው ሁለተኛውን ዙር የተፈጥሮ ጋዝ መውጫ ፕሮጀክት ግንባታ መጀመሩን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
ፕሮጀክቱ ከፈሳሽ ተፈጥሮ ጋዝ ምርት በተጨማሪ፣ 1000 ሜጋ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም አለው ተብሏል። የተፈጥሮ ጋዙ ኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለጀመረችው የክሪፕቶ-ማይኒን ኃይል ሽያጭ ግብዓት እንደሚሆን ተጠቁሟል። እንዲሁም በመተሳሳይ ጊዜ የግንባታ መሰረት ድንጋይ ለተጣለለት የማዳበሪያ ፋብሪካ የግብዓት ምንጭ ሆኖ ያገለግላል ተብሏል። በተመሳሳይ የዩሪያ ማዳበሪያ ፋብሪካ እና የነዳጅ ማጣሪያ ፋብሪካ ግንባ መሰረት ድንጋይ ተጥሏል።
በአራት ዓመት ገደማ ይጠናቀቃል ተብሎ የሚጠበቀው የማዳበሪያ ፋብሪካና የነዳጅ ማጣሪያ ፕሮጀክቶች 10 ቢሊዮን ዶላር ፈሰሰ ይደረግባቸዋል ተብሏል። የማዳበሪያ ፋብሪካ እና የነዳጅ ማጣሪያ ግንባታ ፕሮጅክት በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ በጋራ ባለቤት የተያያዘ ነው። ሁለቱም ፕሮጀክቶች በውጭ ባለሀብቶች የተያያዙ ሲሆን፣ የማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ በናይጄሪያ ዳንጎቴ፣ የነዳጅ ማጣሪያው ደግሞ በቻይና ባለሀብቶች የተያያዘ ነው።









